Letter from Sidama civilians to Ethiopian federal prosperity party leaders

የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርና ብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት
ለብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕረዝዳንቶች
ለኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ
አዲስ አበባ
ለብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት
በያሉበት

ጉዳዩ፡- አቤቱታ ስለማቅረብ ይሆናል፡፡
ከላይ በርዕሱ እንደተገለፀው ይህንን ማመልከቻ አሰናድተን አቤቱታውን ያቀረብን አካላት በሲዳማ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች የምንገኝ ነዋሪዎች ስንሆን ከተለያዬ ማህበራዊ መሰረት የተወጣጣን ግለሰቦች ነን፡፡ የአቤቱታችን መሰረታዊ ጭብጭ የሚሆነው የክልሉ መንግስት የየደረጃው አመራሮች እና መዋቅሩ በተለያየ መንገድ ህዝባችንን እየበደለ መሆኑን ተገንዝበን፣ አስተዳደራዊ በደሉን በግልጽ ለሚመለከተው አካል አቅርበን ፍትህን ለማግኘት በማሰብ ነው፡፡
በክልላችን የምታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የልማት እጦት፣ መዋቅራዊ ሌብነት እና የጎሰኝነት ችግሮች የለውጥ መንግስታችንን እና ህዝባችንን እየጎዳ ያለ መሆኑን ተገንዝበን በባለፉት ዓመታት ትግል ስናደርግ ቆይተናል፡፡ የአስተዳደር አካላት በየፊናው ችግሮቹ አሉ እያሉ የምታገሉ ግለሰቦችን ለመጉዳት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና ፣ በክልሉ ያለው ህዝብ አሁን ባለው አመራር ቲም ደስተኛ ባለመሆኑ አንድም ጊዜ ሳይታገስ በሰላማዊ መንገድ ስሜቱንና ቅሬታውን እየገለፀ፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለውን መረጃ ለሚመለከታቸው እያቀረበ ትግሉን ቀጥሏል፡፡
በመሆኑም በዚህ ሰነድ ውስጥ በዝርዝር ያስቀመጥናቸው ጉዳዮች የሲዳማ ክልል ነባራዊና ህልናዊ ሁኔታዎችን የሚገልፁ ተጨባጭ ችግሮቻችን ስለሆኑ የሚመለከታቸው የመንግስትና የፓርቲ አካላት በአትኩሮት ተመልክተው እንዲፈቱሉን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር

  1. መግቢያ
    በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ታሪክ ውስጥ የሲዳማ ህዝብ ድርሻ የአንበሳውን ስፍራ ይይዛል፡፡ የሲዳማ ህዝብ አንድም ጊዜ በገዥዎች የሚደርስበትን ጭቆናና በደል አሜን ብሎ ተቀብሎ አያውቅም፡፡ ከአፀዎቹ ጀምሮ በተለያየ መልክ የሚገለጽ በደል፣ ተፅዕኖ እና ሰቆቃ ስደርስበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ የሲዳማ ህዝብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ተፅዕኖዎች ስደርስበት የኖረ ህዝብ ነው፡፡
    ነገር ግን የሲዳማ ህዝብ፣ እንደሌላው ብሄረሰብ፣ አንድም ጊዜ ጭቆናውን አሜን ብሎ ተብሎ አያውቅም፡፡ መብቶቹን ለማስጠበቅና ለማረጋገጥ በተለያየ ጊዜ የተደራጀና ያልተደራጀ ትግል ስያደርግ ቆይቷል፡፡ ከ1969 መጨረሻዎቹ ጀምሮ የትጥቅ ትግልንም አድርጓል፡፡ የ’ደርግ’ ሥርዓተ መንግስትን ግብዓተ መሬቱን በማውረድ ሂደት ውስጥ እንደ ሌሎች ብሄረሰቦች የማይተካ ሚናውን ተጫውቷል፡፡ የደርግ መንግስት ተሸንፎ በኢህአዴግ መሪነት የሽግግር መንግስት ሲቋቋም ሲአንን ጨምሮ ሌሎች የሲዳማ ህዝብ የነጻነት ድርጅቶች የሽግግር መንግስት አካልም ነበር፡፡
    ዳሩ ግን የሽግግር መንግስት ቆይታ ጊዜ ተጠናቅቆ የክልል አደረጃጀቶች ሲዋቀሩ የሲዳማ ህዝብ የአጥንትና የደም ዋጋ የከፈለበትን ክልል የመሆን ወይም ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዕድል ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በኃይልና በጡንቻ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ታጉሮ ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ከእነዚሁ ጋር ስተዳደር ነበር፡፡ የሲዳማ ህዝብ በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ቢሆን ላፍታም ሳይዘናጋና ወደኋላ ሳይመለስ ክልላዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ስታገል ኖሮአል፡፡ በዚህም በርካታ ልጆቹን ገብሯል፡፡ የክልል አደረጃጀት እንዳይነሳ በተለያየ መንገድ ሲደፈጠጥ ስለነበር ለዚህ አጀንዳ የሚታገል ኃይል በተለያየ መልክ የሚገለጽ ተጽዕኖ ስደርስበት እንደነበር እሙን ነው፡፡
    እንደ ሀገር አጋጥሞን የነበረው ኢኮኖሚያዊ ውድቀት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የልማት እጦት በተለይም የወጣቶች ቁጣና ቢሶት የወለደው የለውጥ ኃይል በየደረጃው የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ የተደራጀ ትግል አድርጓል፡፡ ትግሉ የጀመረበት ጊዜ ትክክለኛነት እደተጠበቀ በይፋ ሪቫይቫል ሆኖ የተለኮሰው ግን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ብዙም አያከራክርም፡፡ በእነዚህ ወቅቶች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም አጋሪ ድርጅቶች ያሉ ችግሮችን ለማረም ጥልቅ ግምገማ አድርገው የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም እያስቀመጡ ለመሄድ የሞከሩ ቢሆንም ችግሮቹን መፍታት አልቻሉም፡፡ በወቅቱ የሲቪክ ማህበራት፣ የማህበራዊ ሚዲያ አንቅዎች፣ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ሌሎች አካላት አሁን ያጋጠመንን ችግር ኢህአደግና በእሱ የሚመራው መንግስት መፍታት አይችልም ሪፍርም ወይም ለውጥ ያሳፈልጋል የሚለውን አቋም እንደገፉበት እናስታውሳለን፡፡
    በመሆኑም በዚህ መልኩ እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የዘለቀው ፖለቲካዊ ንቅናቄ እና የለውጥ ኃይሎች ትግል በየአከባቢው አዳዲስና ነባር ጥያቄዎችን እያቀጣጠለ ኢህአዴግ ሳይወድ በግድ እጅ እንድሰጥ አደረገው፡፡ እንግድህ የሲዳማ ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የትግል ሁኔታዎች ከላይ በተገለፀው መንገድ የሪቫይቫሉ አካል ለመሆን በቃ፡፡ በ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የሲዳማ ህዝብም ውዝፍ ችግሮቹንና ጥያቄዎቹን ለሀገር መሪዎች በይፋ በማቅረብ የተለመደውን ትግል በሰላማዊ መንገድ አጠናክሮ በመቀጠል ለጥያቄዎቹ ምላሽ አግኝቷል፡፡ በዚህ ወቅት የሲዳማ ተወላጅ የሆነው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነዋሪዎች በክልል የመደራጀት አጀንዳን የራሱ በማድረግ ለማሳካት ጥረት እንዳደረገም ይታወቃል፡፡ ክልል ሆኖ መደራጀት እንደሚፈልግና ክልላዊ አደረጃጀት ሲኖረው ሊያስገኝለት የሚችለውን ብሄራዊና ክልላዊ ጥቅምና ጉዳት ተንትኖ በማስረዳት እንደሀገር ለአጀንዳው ተገቢ ስፍራና እውቅና እንዲሰጠው በማድረግ ትግሉ በይፋ የመለኮስ ስራዎችንም ተሰርቷል፡፡
    ህገመንግስትን መሰረት በማድረግ የተደረገው ትግል ጥያቄው በሀገር ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ እና የህዝባችን የዘመናት እሮሮ፣ ሀዘንና ትካዜ እንዲቆምም አስችሏል፡፡ ጥያቄው በ2011 ዓ.ም በህዝቤ ውሳኔ መቋጫውን እንዲያገኝም ተደርጓል፡፡ የህዝቤ ውሳኔ አፈጻጸምን ተከትሎ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግልጽ ደብዳቤ በመጻፍ አንድም ይፋዊ የስልጣን ርክክብ እንዲከናወን ያደረጉ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ አዲሱ የሲዳማ ክልል የኢፌድሪ የፌደረሽን አካል እንዲሆን የምያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችም እንዲሟሉ አድርገው አልፈዋል፡፡
    አዲሱ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በ2012 ዓ.ም መጨረሻዎቹ አከባቢ በይፋ እንድደራጅ የምያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ክልላዊ አደረጃጀት እንድኖረው ተደርጎአል፡፡ ከነችግሮቹም ቢሆን ለሲዳማ ህዝብ የራሱ የሆነ ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔዎች እንዲኖሩትም ተደርጓል፡፡ የክልል ቢሮዎች፣ አጄንሲዎች እና ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙም ተደርጓል፡፡ በጥቅሉ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ተመስርቶ ስራውን በይፋ ጀምሯል፡፡
    ይሁንና የ’ሲዳማ ክልል’ ገና ከመነሻው የግለሰቦች፣ ለህዝብ ተጠቃሚነት በማይተጉ ሰዎች የተወከለ ሆኖ ተደራጀ፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ መንገድ ከስልጣን የተወገዱ እና በየደረጃው ስሜት የያዙ ሰዎች ተመልሰው የአደረጃጀቱ አካል በመሆናቸው በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጠረ፡፡ የክልሉ “ፕሬዝዳንት”ን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ክልላዊ ስልጣን የያዘው ኃይል በዚህ መልኩ በየደረጃው ከስልጣን የተባረረና የወገንተኝነት ችግሮች ያሉባቸው እደሆኑ ይታወቅ ነበር፡፡ በመሆኑም በርዕሰ መስተዳደሩና በአባላቱ የሲዳማ ህዝብ ደስተኛ ሳይሆን ቀረ፡፡
    የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት የታገለው ትግልና የትግሉ ፍሬ በአቋራጭ እንደተነጠቀበት በመገንዘብ፣ በዚህ ዙሪያ ያለበትን ቅሬታና ስሜት በተለያየ መንገድ ስገልጽ ቆይቷል፡፡ ከዚህም መነሻ የሲዳማ ህዝብ የ”ወላድ መካን” ሆኛለሁ፣ እኔን የምመስል መሪ አላገኘሁም እና አሁን በአቋራጭ ስልጣኑን የተቆናጠጠው ኃይል ጥቅመንና መብቶቼን የሚያረጋግጥልኝ ባለመሆኑ ታግዬ ማስተካከል አለብኝ የሚል አቋም ውስጥ ገና ከክልል ምስረታ ማግስት ጀምሮ ለመግባት ተገዷል፡፡
    በመሆኑም በዚህ ሰነድ፡-
    • የክልሉን ስልጣን የተቆናጠጠው አመራር ቡድን ከአንዳንድ አካላት ጋር የነበረውን ትስስርና የአደረጃጀት ሁኔታውን አጠር ተደርጎ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
    • በዚህ ሰነድ ውስጥ በየደረጃው ያለ አመራር እና የህዝብ ሁኔታ በተለይም የወጣቶች ሁኔታ በአጽንኦት ተመልክቷል፡፡
    • በአሁኑ ወቅት የሲዳማ ክልልን እየመራ ያለው ኃይል በክልሉ ህዝብ ላይ እያደረሰ ስላለው አስተዳደራዊ በደል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች/በፍትህና በፀጥታ መስክ/ ፣ የሌብነቶቹ መልኮች እና የህዝብ ስሜት ለሚመለከተው አካል ለማሳየት ጥረት ተደርጓል፡፡
    • በዚህ ሰነድ ውስጥ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የከተማ ልማት፣ የፍትህ እና የፀጥታ መዋቅር ሁኔታ አጠር ብሎ ቀርቧል፡፡
    • በተያያዘ በፖለቲካ መስክ አዲሱ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ አመሰራረት ሁኔታ፣ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች በግምገማ መልክ የሰነዱ አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡
    ስለሆነም ይህንን ሰነድ የምያገኝ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የመንግስት አካላት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሰነዱን መነሻ በማድረግ የሚሰጠውን አስተያየትና አቅጣጫ ተቀብለን ተፈጻሚ ለማድረግም ያለንን ዝግጁነት ስንገልጽ በሙሉ መተማመን ነው፡፡
  2. የሰነዱ ዓላማ
    2.1 ዓላማ
    • በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዉስጥ ያሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ተንትኖ በማሳየት የሚመለከታቸዉ የመንግስትና የፓርቲ አካላት መረጃ እንዲያገኙና አስፈላጊዉን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ታሳብ ተደርጓል፡፡
    • የሰነዱ ሌላኛው ዓላማ በሲዳማ ክልል ደረጃ ሹመኞች የፈጠሩትን የተዛባና የተንሸዋረረ የአስተዳደር ስርዓትን በሰላማዊና በሰለጠነ አኳሃን እንደ ፓርቲ አባላት ታግሎ በማስተካል ለልማታዊና ለብልጽግና ጉዞአችን መልካም መደላደል መፍጠርን መዕከል ያደረገ ሆኖ በዚህ ዙሪያ የሚስተዋሉ ኋላቀር፣ ጎታች እና የወንድማማችነት እሴትን የምጎዱ አስተሳሰቦችን በተባበረ ክንድ መድፈቅ ይሆናል፡፡
    • ከዓላማዉ በመነሳት ይህንን ሰነድ የሚያዳብሩ የተለያዩ መረጃዎችንና ኢንፎርሜሽኖችን ካለዉ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ የተሟላ ሰነድ በማድረግ የመንግስትና የፓርቲ አመራር አካላት ምሉዕ ግንዛቤ ኖሮአቸዉ እርምጃ እንዲወስዱ ለማገዝ የተዘጋጀ ሰነድ ነዉ፡፡
    • ስለሆነም ይህንን ሰነድ የሚያገኝ የመንግስትና የፓርቲ አመራር አካላት በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዉስጥ ከክልል ቢሮዎች እስከ ወረዳ ድረስ የምፈፀመዉን የኪራይ ሰብሳቢነት እና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ጠንከር ያለ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ይወስዱሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
    2.2 የሰነድ ተደራሽነት
    • ይህ ሰነድ በዋናነት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንድደርስ ታምኖበት የተዘጋጀ ስሆን ፣ በተመሳሳይ ሌሎች በፌደራል ደረጃ ያሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አካላትም እንዲያገኙ፣ ከዚህ በመነሳትም በሲዳማ ክልል ያለውን ወይም የምስተዋለውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በመገንዘብ በየፊናቸው እርምጃ እንድወስዱ ተጨማሪ መረጃ ለማቅረብ ነው።
    • ይህ ሰነድ በተለየ መልኩ ለብልፅግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አካላትም እንድደርስ የተፈለገበት ምክንያት፣ በክልላችን ያለው አስተዳደራዊ በደል ለማስወገድ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ትግልና ትብብር ስለሚሻ ነው።
    • ዋነኛ ፍላጎታችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአካል ተገናኝተን መነጋገር ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ሀሳብ መነሻ አድርገን የፌዴራል መንግስት ተቋማት ኃላፊዎች ቢሮዎችን ለማንኳኳት ጥረት አድርገናል፡፡ የፌደራል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ቢሮ ጭምር በአካልና በስልክ ደርሰን ያሉብንን ችግሮች ለማሳወቅ ጥረት ያደረግን ቢሆንም አልተሳካልንም፡፡ ስለሆነም ከዚህ መነሻ አንደአማራጭ የወሰድነው በዚህ መንገድ ሰነድ አዘጋጅተን ለሚመለከታቸው አካላት ለማሳወቅ ብቻ ነው፡፡
  3. አሁን ስልጣን ላይ ያሉ አመራር አካላት አመጣጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች፡ ይህ ኃይል ከመነሻውም በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነትን ያገኘ አልነበረም፡፡ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አመራር ቲም እንደሀገር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በየአከባቢው የነበረውን እንቅስቃሴ እንደምቹ አጋጣሚ በመውሰድ በየሆቴሉ እየተሰባሰቡ በወቅቱ የነበረውን አስተዳደር አካሉን ለመጣል ሲሰራ ነበረ ነው፡፡ በመሰረቱ የአሁኑ ርዕሰ መስተዳደር በ2008 ዓ.ም በተደረገ ግምገማ በሌብነት እና በመሬት ድሌላ ተግባሩ ተገምግሞ ከፍተኛ የዲስፕልን ጥሰት በመፈፀሙ ከኃላፊነት ተነስቶ ነበር፡፡ ልክ ከኃላፊነት እንደተነሳ፣ ከእሱ ጋር ተገምግመው የተነሱትን አሰባስቦ በዞኑ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖር እና ዳግም መንበረ-ስልጣኑን መቆናጠጥ በሚቻልበት ስልቶች ዙሪያ ስመክር እንደቆየም ይታወቃል፡፡ የግለሰቦቹ ዋነኛ ፍላጎትና ዒላማ የስልጣን ጥማት እንደሆነና ያለአግባብ ከስልጣን ኮርቻችን ወርደናል የሚለውን ሀሳብ በመያዝ እንደሆነ በወቅቱ የዚህ አደረጃጀት አባል የሆኑ ግለሰቦች ያስረዳሉ፡፡
    በመሆኑም ይህንን አስተሳሰብ መነሻ በማድረግ የተጠነሰሰው አደረጃጀት እየዋለ እያደረ በ2009 ዓ.ም ጠንከር ያለ ስብስብ እየሆነ መጣ፡፡ በየሆቴሉ እየተሰባሰቡ በ2010 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ለተፈጠረው ሁኬት፣ ብጥብጥ፣ ለንብረት ውድመት እና ለሰው ህይወት መጥፋት አቀጣጣይ ለመሆን እንደበቃም ይነገራል፡፡ በተመሳሳይ በ2011 ዓ.ም የክልል አደረጃጀትን ተገን በማድረግ እና በህቡዕ በኤጄቶ ጉያ ውስጥ በመወሸቅ የራሱን እንጎቻ እያበሰለ መክረሙም ይታወቃል፡፡ በአቶ ደስታ ሌዳሞ መሪነት በወቅቱ የዞን ስልጣን የያዘው ቲም ቁልፍ ተልዕኮው የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት አጀንዳውን መቀልበስ፣ በዚህ ሂደት ሁኬትና ግርግር ተፈጥሮ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ አመራር አካላት/ለእነሱ የማይመቹትን/ እንድጠየቁ ማድረግ ነበር ዓላማቸው፡፡ የሲዳማ ክልል ጉዳይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሳል አመራር ሰጪነት እና በፓርቲው ወሳኝ እርምጃ ዳር እንዲደርስና ፍሬ እንድያፈራ መደረጉ እሙን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አባቶች እና የተለያዩ አካላት፤ በጥቅሉ መላው የሲዳማ ህዝብ ለክልል ጉዳይ ዋጋ ከፍሎ አልፏል፡፡ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል አድርጓል፡፡ ህዝባችን፣ ምንም ዓይነት ሁኬትና ብጥብጥ ሳይኖር በሰላማዊ መንገድ መንበረ ስልጣኑን በእጁ ማስገባት እንደሚችል አውቆ በሳል ትግል አድርጓል፡፡ በዚህም ዓለምን ያስደመሙ ግዙፍ ሰልፎችን ከሀዋሳ ጀምሮ በየአከባቢው ተደርጓል፣ መሳጭ እና ምንልባትም እንደ እኛ ድሃ በሆኑ ሀገራት ያልተሞከረውን ያካ/የመላ የሲዳማ ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ/ ተከናውኖም አልፏል፡፡ ሁሉንም ሂደቶችና እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ መንገድ የታለፈ ቢሆንም የተከፈለው ዋጋ ግን በቀላሉ የሚገመት አልነበረም፡፡ ትግሉን ለመቀልበስ የመጡ የእነ አቶ ደስታ ሌዳሞ ቡድኖችም በህዝቡ ማዕበል ተውጠው ጉዳዩን የሚያስፈጽሙ ሆነው አልፈዋል፡፡
  4. የአመራር እና የህዝብ ሁኔታ
    4.1 የአመራር ሁኔታ
    4.1.1 የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ፡-
    ይህ ኮሚቴ በዋናነት ክልላዊ መንግስቱን የማስተባበር ኃላፊነት የተሰጠው ቁልፍ የአመራር አካል ነው፡፡ አመራር አካሉ በክልሉ ውስጥ የመንግስትንና የድርጅትን ስራዎች በበላይነት የመምራት፣ የማስተባበር፣ ልማትና መልካም አስተዳደር እንድረጋገጥ መስራት፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ቶሎ መፍታትና ማረም፣ የክልሉን ህዝብና መንግስት በመወከል ከፌደራል መንግስት ጋር ቅርበት ያለው ግንኙነት ማድረግ፤ በጥቅሉ በክልላዊ መንግስት ውስጥ ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲኖር፣ ኋላቀርነት እንዲቀንስና እንዲጠፋ፣ ቴክኖሎጂን የሚቀበልና የሚተገብር ህ/ሰብ በተለይም ወጣት ትውልድ እንዲፈጠር መስራት ቁለፍ ተግባራቸው ስሆን የፓርቲ ስራዎችንም ቀዳሚ ተግባር አድርገው የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ይሁንና ይህ ኃይል ከመነሻውም መርህ አልባ እና መላ-ቅጡ የጠፋበት ኮሚቴ መሆኑ ታወቀ፡፡ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ ሁሉም የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የአቅምና የአስተሳሰብ ችግር ያለባቸዉ፣ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸዉ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት የተተበተቡ፣ ህዝቡን በየፊናዉ ተግባር ዉስጥ ማስገባት ያልቻሉና የተንሳፈፉ፣ በጎሴኝነት አስተሳሰብና ተግባር የተለከፉ እና ህዝባዊ ወንገንተኝነታቸዉ የላሸቄ ከመሆኑ የተነሳ በአሁኑ ጊዜ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዉስጥ ያለዉ ህዝብ የ‹‹ወላድ መካን›› የመሆን ዕድል አጋጥሞታል፡፡ አመራሩ በክራይ ሰብሳብነት ችግሮች የምታማ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ሌባ መዋቅር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቁጥር አንድ የመክበሪያ ምንጭ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የሀዋሳ ከተማ መሬት አስተዳደርና የማስተላለፍ ሂደቱ ህገወጥነትን የሚያጎላና በተጨባጭም ሌብነት ያለበት መሆኑ (ተጨባጭ መረጃ መቅረብ ይቻላል)፣ የእሸት ቡና መፍልፈያ እንዱስትሪ ፈቃድ አሰጣጥ (ያለጥናት የተሰጠ ከመሆኑም በላይ ከእያንዳንዱ ግለሰብ 300ሺ ብር እየተወሰደ የተሰጠ እና ከፍተኛ አመራሩ ለራሱ ጭምር እየወሰደ ሌለላው የሚሰጥበት መሆኑ፣ የገጠር መሬት በኢንቨስትሜንት ሽፋን እየተቸረቸረ ያለ መሆኑ(ማጭሾና ወንዶ ገነት አከባቢ) እና በየደረጃው ከአመራር ምደባ ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ሌብነት (ጉቦ) ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡
    o ስለሆነም የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሁሉንም ተግባራቶች የሚያየዉ ከክራይ ሰብሳቢነት መነጽር አንፃር ብቻ መሆኑን ስንገልጽ በከፍተኛ ሀፍረት ውስጥ ሆነን ነዉ፡፡ የሲዳማ ህዝብ፣ ለዘመናት የታገለዉ ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና መዋቅራዊ ችግሮቹ እንዲፈቱለት በማሰብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በእርግጥም የራሱን ክልላዊ መንግስት መስርቷል፡፡
    o ይሁንና አዲሱን ክልላዊ መንግስቱን እንዲመሩና እንዲያስተባበሩ ከብልጽግና ፓርቲ ሀላፊነት የተሰጣቸዉ አስተባባሪ አካላት የተንሳፈፉና ህዝባዊ መሰረት የሌላቸዉ ከመሆናቸዉ የተነሳ አንድም፣ ህዝባችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርግ ነባራዊና ህልናዊ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፣ በሌላ ጎን ህዝባችን በብልጽግና ፓርቲ ላይ እምነት እንዲያጣ የሚያስገድድ ህልናዊ ሁኔታ እንዲፈጠርበት ሆኖአል፡፡
    o ከዚህ መነሻ የ‹‹ሲዳማ ህዝብ ክልል ሆኗል እንጂ ክልሉን የሚመራዉን አመራር አላገኘም›› የሚለዉን ጠላትም ወዳጅም ያነሳል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ትልቁ ማሳያ የሚሆነው የሲፌፓ/የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ መመስረት ነው፡፡ ወላጆችም ሆነ ወጣቶቹ በየደረጃው በአመራሩ ተጨባጭ ድርጊት፣ በተለይም በክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ተስፋ በመቁረጡ እና አስተባባሪ ኮሚቴውም በዚሁ ጉዳይ ትርጉም ያለውን ትኩረት ባለመስጠታቸው በብልጽግና ጉያ ስር የነበሩ ወጣቶችና ወላጆች አዲስ ፓርቲ ወደመመስረት ገብተዋል፡፡
    o የሲፌፓ ፓርቲ እንዲመሰረት ዓይነተኛ ሚና የተጫወተው የክልሉ ከፍተኛ አመራር ነው፡፡ ፓርቲያችን ፣ የህዝባችን ባለውሌታ መሆኑ እየታወቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ቆርጦ ሌላ ፓርቲ እንዲያስብ ያደረገው ምክንያት የመልካም አስተዳደር እጦት እና በቸልተኛ መዋቅር የሚመራ ክልል በመሆኑ ነው፡፡ የ‹‹ሲዳማ ህዝብ ክልል ሆኗል እንጂ ክልሉን የሚመራዉን ቆራጥ፣ ትሁት ፣ ዴሞክራቲክ አመራር አላገኘም›› የተባለበት አንደኛው ምክንያት፣ አቶ ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ ክልሉን እንድመሩ ስምሪት የተሰጣቸዉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለሲዳማ ህዝብ የታገሉ አይደሉም፣ አደናቃፊዎች ነበሩ፡፡ በሲዳማ ህዝብ ዘንድ እነርሱ የታወቁት በሌብነትና በጎሴኝነት ብቻ መሆኑን (በተለይም በኮንትሮባንድ ንግድ የከበሩ መሆናቸዉን ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ህዝብ የሚያውቀውና ፀሀይ የሞቀዉ ጉዳይ መሆኑ) እና ወዘተ….. ጉዳዮችን በማንሳት ህዝቡ የሚያጉረመርምባቸዉ አካላት ስለሆኑ ያለባቸዉ ነቀፈታ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ስለሆነም ከፍ ተብሎ የተብራሩና የተገለጹ ችግሮችን ለማወቅ ከተፈለገ በክልሉ ዉስጥ በገጠርም ይሁን በከተማ ያሉ ወጣቶችን፣ እናቶችን፣ አባቶችን፣ የሀይማኖት መሪዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በሚፈለግ ዘዴና መንገድ በመጠየቅ ወይንም እነዚህን አካላት ተጠቅሞ ስዉርና ግልጽ መረጃ በመስራት ማረጋገጥ የሚቻል ይሆናል፡፡ በተለይም የወጣቱን ክፍል ለይቶ በማወያየት ያለዉን ችግር መለየትና ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የ‹‹ሲዳማ ህዝብ ክልል ሆኗል እንጂ ክልሉን የሚመራዉን አመራር አላገኘም›› የተባለበት ሁለተኛው ምክንያት፣ አቶ ደስታ ሌዳሞና መዋቅራቸዉ ወደ መንበረ ስልጣኑ የመጡበት መንገድ ጠማማ/ ኮራፕቲዲ (Corrupted) መሆኑ ነው፡፡ ሰዎቹ፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራር አካላትንና የደህንነት ክፍሉን በማሳሳት የመጡ መሆናቸዉን በስፋት ይነገራል ብቻ ሳይሆን ነውም፡፡ በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆን ይፈለግ የነበረው ሌላ አካል ነበር፡፡ ያነ ሌላ አካል ርዕሰ መስተዳደር ሆኖ ቢሆን ኖሮ ለዚህ አደጋ አንጋለጥም የሚል ቁጭትና ሀዘን በህዝቡ ዘንድ ይነሳል፡፡
    ሁሉም የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በመሰረታዊነት የአስተሳሰብ፣ የማስፈፀም አቅም እና የዝግጁነት ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡
    o ለዚህም ማሳያ የሚሆነዉ በክልሉ ዉስጥ በየደረጃዉ የፓርቲዉ አደረጃጀትና አሰራር እንዲጠናከር መስራት የማይችል ተንሳፋፊ አመራር ያለበት መሆኑ ነዉ፡፡ በክልሉ ዉስጥ ያሉ የፓርቲዉ አደረጃጀቶች (ህዋስ፣ መሰረታዊ ድርጅቶች፣ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች በተለይም ሊጎች) በአሰራራቸዉ መሰረት እየተገናኙ የሚገመግሙና የሚወያዩ አይደሉም፡፡ ሁሉም ነገር የይድረስ ፣ ለብ ለብ ብቻ ነው፡፡
    o የአባላት አስተሳሰብና አቅም ግንባታ ደካማ ነው፡፡ በየማህበራዊ መሰረቱ ያለ አባል የመልካም አስተዳደር ችግር እንድተች አይፈለግም፣ በየቢሮው፣ በየመምሪያው ወይም በየወረዳው የሚስተዋሉ ሌብነቶችን ወይም የፍትህ ችግሮችን ደፍሮ እንድናገር አይፈለግም፣ የተሸማቀቀ አባል ነው ያለው፡፡
    o በሁሉም ወረዳዎች ማለት በሚቻል ደረጃ የአባላት ግንባታ አፈጻጸም ደካማ እንደሆነ የተለያየ ማሳያ በማቅረብ መሞገት ይቻላል፡፡ የህዋስ እና የመ/ድርጅት አደረጃጀቶች አመራር አባላትን ተቋማዊ አድርጎ አይከታተልም፡፡ የየጽ/ቤቱ፣ የመምሪያ እና የቢሮ ኃላፊዎች አባላትን ይፈራሉ፡፡ በየተቋማቱ የአመራሮች እና አባላት/ሰራተኞች መካከል ያለ ግንኙነት ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡
    ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻና ባለቤት አለዉ፡፡ መነሻዉም ባለቤቱም የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራር ነዉ፡፡ በድምሩ የችግሮቹ አልፋና ኦሜጋ አመራሩ ነው፡፡ አያደርገዉና አሁን በዚህ ጊዜ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ብደረግ የብልጽግና ፓርቲን አደጋ ላይ የሚጥልና ህልዉናዉን ሊጎዳ የሚችል ዉሳኔ ከህዝቡ በተለይም ከወጣቱ ህ/ሰብ ክፍል ሊወሰን እንደሚችል ነባራዊና ህልናዉ ሁኔታዎች በተጨባጭ ያሳያሉ፡፡ ይህንን ሀሳብ የምያጠናክር የነባራዊ ሁኔታ ይሁን የህሊናዊ ሁኔታ ገጾችን በዝርዝር ማቅረብ ይቻላል፡፡
    4.1.2 የቢሮ ኃላፊዎች ሁኔታ በሚመለከት
    በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ደረጃ አስፈላጊ የሚሆኑ ቢሮዎች፣ ኤጄንሲዎችና ኮሚሽኖች በአዋጅ ተቋቁሟል፡፡ የተለያዩ ኤጀንሲዎችና ኮሚሽኖችም በተመሳሳይ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ ሁሉም ቢሮዎች እንደየሁኔታቸው የአመራር ምደባና ስምሪት እንዲኖረው የተደረገ ቢሆንም የምደባ አፈጻጸሙ ጉራማይሌና ወጣገባ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ በየቢሮው ከተመደቡ አመራሮች ውስጥ የተወሰኑት ነባር አመራሮች፣ የተወሰኑት አዳዲሶች ስሆኑ ቀሪዎቹ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሾሙ ናቸው፡፡ በዚህ ሰነድ አመራር ኮሚቴውን ለመተቸት ተፈልጎ አይደለም፡፡ ያለውን ጉድለት አጉልቶ በማሳየት ያሉ ግድፈቶች እንዲታረሙ ለማበረታታትና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ብቻ ነው፡፡ ምደባ ወስዶ በአቅሙ ልክ ወደ ተግባር የገባው አመራር ቲም ከቻለ የተሰጠውን ኃላፊነት ልወጣ ይችላል፣ አሊያም ልንገዋለል ይችላል፡፡ በተግባር ውስጥ በግል ጥረቱና መነሳሳት አቅም ገንብቶ በላቄ ደረጃ የተሻለ አፈጻጸም ሊያስመዘግብ የሚችል ግለሰብ ይታጣል የሚል ግምትም የለንም፡፡ ዳሩ ግን የአመራር ምደባው ብቃትን፣ የሲዳማ ህዝብ ስነልቦናና ለመለወጥ ያለውን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አለመሆኑን ለማመላከት ብቻ ነው፡፡ ከቢሮ ኃላፊዎች ጀምሮ በየደረጃው የተመደበው አብዘኛው አመራር/ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ውጭ/ በተለያየ ጊዜ በስነምግባር ጉድለት፣ በአፈጻጸም ዝቅተኛነት፣ በሌብነት፣ በወዘተ ጉድለቶች ተገምግሞ የተባረሩ ግለሰቦች የተሰባሰቡበት አሃድ ነው፡፡ አመራር ቲሙ፣ በሲዳማ ክልል ያለው የመልማት ፀጋን ለይቶ እንደየአግሮ-ኢኮሎጂው አቅዶ ፣ ለምሳሌ፡- በግብርና እና በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት አርሶ አደሮችን ውጤታማ ማድረግ የቻለ አይደለም፡፡ በትምህርትና በጤና ልማት ስራዎች የተሳካለትም አይደለም፡፡ በከተማ ልማት፣ በፋይናንስ አስተዳደር ዘርፎችም የከፋ ሌብነትና ጋጠወጥነት የሚስተዋልበት መሆኑን በተደጋጋሚ ለተለያዩ አካላት መረጃ ስናቀርብ ከርመናል፡፡ አመራሩ፣ ለስልጣን የመጣበት መንገድ የተዛባ ስለነበር መለያ ትኩረቱ ለሌብነት ነው፡፡ በየቢሮው የተመደበ አመራር በጉቦ፣ በጋብቻ ትስስር፣ የደም ላቦራቶሪ ተሰርቶለት በዚያ ውጤት መነሻነት ወይም በጓደኝነት መረብ መነሻነት የተመደበ በመሆኑ የመጣበትን ዓላማ ብቻ ለማሳካት የሚታትር ነው፡፡ በየዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት ትኩረት አድርጎ የሚፈጽም ባለመሆኑ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው ህዝባችን፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በስራ አጥነት በሽታ ይሰቃያል፡፡ በፍትህና በደህንነት መስኮች ያለው ችግር ብዙ ነው፡፡ የአመራራችን ሌላኛው ችግር ፓርቲያችንን የሚደግፍና የሚያጠናክር አቅም ወይም ዝግጁነት የጎደለው መሆኑ ነው፡፡ ሹመኞቹ ፣መኪናቸውን ሌላ ሰው እያሽከረከረላቸው፣ በአጃቢ ጋጋታ እና በስናይፔር እጀባ የምንጎባለሉ፣ ወደ ህዝብ የማይጠጉ፣ የፓርቲ አደረጃጀቶችን የማጠናከር ፍላጎትና አቅም የሌላቸው – ተንሳፋፊ ሰዎች ናቸው፡፡ በመ/ቤቱ ያለችውን ህዋስ በድፍረት በቢሮአቸው ያለችውን ህዋስ ለማወያየት ሞራል የሌላቸው የቢሮ ኃላፊዎች በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡
    4.1.3 የወረዳ አመራር ሁኔታ በአጭሩ
    በተለምዶ የወረዳ አመራሮች ለህዝቡ ቅርብ ነው፣ ከቀበሌ መዋቅር ጋር ሆኖ የመንግስትና የፓርቲ እቅዶችን ወደታች ለማውረድ እንደድልድይ የሚያገለግል ወሳኝ ኃይል መሆናቸውን አብዘኛዎቻችን የምንስማማ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ኃይል ባለፉት ጊዜያት የሲዳማ ክልል እውን እንዲሆን ያላሰለሴ ትግል አድርጓል፡፡ ችግሮቹ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም ወረዳዎች ያለ አመራር አሃድ የተሰጠውን ተግባር ወደታች ለማውረድ የሚጥር እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ይሁንና ይህ ቲም እንደላይኛው አመራር የራሱ ችግር ያለበት ነው፡፡
    o ክራይ ሰብሳብነትና የሌብነት ችግሮች፣ የውጤታማነት ችግሮች፣ ጎሰኝነትና እርስ በርስ የመጠቃቃት አባዜ፣ የክልሉ ቁልፍ አመራር ከመርህ ውጪ ስለሚንቀሳቀስ ሁሉም የወረዳ አመራር ማለት በሚቻል ደረጃ የፓርቲ ዲሲፕልን የሚገዛውና ለፓርቲ መርህ የሚገዛ አመራር ቲም አለመሆን (በተገቢው ያልተገራ መዋቅር መሆኑ)፣ ለወጣቶች ተጠቃሚነት የማይተጋና ለግል ምቾቱ የሚተጋ ኃይል፣ በገጠር የወል መሬቶችን የሚቸበችብ፣ በከተማ በማዘጋጃ ቤት ስር ያሉ መሬቶችን በጨረታና በምደባ ሽፋን የሚቀራመት፣ በኮንትሮባንድ ንግድ የተለከፉ፣ የቀበሌ ቤቶች ቁልፍ እየሸጠ ለፍትሃዊነት ደንቃራ የሆነ መዋቅር እና ህዝባዊ ወገንተኝነት የለሌው ኋላቀር ቲም ነው፡፡ የወረዳ የፊት አመራሮች፣ በወረዳው ውስጥ ያሉ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በማህበር እያደራጀ በገቢ ማስገኛ መስክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ የተጣለበት ቢሆንም የተሰጠውን ኃላፊነት በትጋትና በታማኝነት መወጣት ያቃተው መሆኑን አሁን በክልሉ ውስጥ በየአከባቢው ከዩኒቨርሲቲ እና ከኮሌጅ ተመርቀው ስራ አጥ ሆነው በቤታቸው የተቀመጡ ወጣቶች ምስክር ናቸው፡፡ በክልሉ ውስጥ በገጠርም ሆነ በከተሞች ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ አለ፡፡ በሁሉም ወረዳዎች ማለት በሚቻል ደረጃ ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ተስፋ ቆርጠዋል፣ ወላጅ አባቶች አዝነዋል፣ እናቶች የሚተክዙ ሆነዋል፡፡ በየወረዳ ያሉ አመራር አካላት ተመላላሽና በተመደቡበት ወረዳ ተተክለው የሚሰሩና ስራውን የሚያስተባብሩ አይደሉም፡፡ ማለትም ወደ በንሳ ዳዬ አቅጣጫ ባሉ ወረዳዎች የሚሰሩ አመራሮች የተወሰኑት ከዳዬ ከተማ እየተነሱ የሚሰሩ፣ የተቀሩት ከይርጋለምና ከሀዋሳ እየተመላለሱ የሚሰሩ፤ በሌሎች ወረዳዎች የሚሰሩ አመራሮች በአብዘኛው ከሀዋሳ እየተመላለሱ የሚሰሩ ናቸው፡፡ መመላለሳቸው ባልከፋ፣ ቁልፉ ችግር በመንግስት በጀትና ተሽከርካሪ የሚመላለሱ መሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም በየወረዳው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለቅሞ የመፍታት ዝግጁነትና ስብእና ያለው ኃይል አይደለም፡፡ ይህንን ሀሳብ እኛ ካቀረብነው በላይ ወደ ታች ወርዶ በተጨባጭ ማድረግ ይቻላል፡፡ በጥቅሉ በሲዳማ ውስጥ ያለው ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች ድፍርስ ናቸው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የጎራ መደበላለቅ አለ፡፡ ሌባውንና ሌባ ያልሆነውን ለመለየት የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች የሉም፡፡ ልማትና መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ ለብልጽግና ፓርቲ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በርግጠኝነት ለመናገር በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት፣ አሰራር እና መርህ አለ ለማለት የሚያስችል ምልክት የለም፡፡ ይህንን ጉዳይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በራሱ መንገድ ማረጋገጥ ይችላል፡፡
    የወረዳ አመራሩም ሆነ የቀበለ አመራር በከፍተኛ ደረጃ ወነው የተሰለበና ቀልቡ የጠፋበት ሆኖአል፡፡
    o በአቋራጭ ለመበልፀግ እና የህዝቡን ሀብት ዘርፎ በሀዋሳ ከተማ የመኖሪያ ቤት ለመስራት የሚያስችል ውጥን ብቻ ይዞ በጉቦና በምልጃ የሚንቀሳቀስ አመራር ቲም ነው ያለው፡፡ ስለሆነም ይህንን ቲም አስተካክሎና አርሞ ወደተስተካከለ ቁመና ማምጣት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡
    4.2 የገጠርና የከተማ ህዝብ ሁኔታ
    የገጠርም ሆነ የከተማ ህዝባችን መለወጥን ይሻል፡፡ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ተቀርፎለት የትሩፋቱ ተጠቃሚ መሆንን ይፈልጋል፡፡ ፍትህ የሰፈነባት፣ ልጆቻቸው ተምረውና ተድረው ለወግ ለማዕረግ ደርሰውላቸው ማየትንም ከልብ ይመኛሉ፣ ይፈልጋሉም፡፡ በድምሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው ደረጃ በደረጃ ተፈትተውላቸው ማየትን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ የሲዳማ ህዝብ፣ እንደሌላው ጭቁን ህዝብ የታገለው በዋናነት ማህበራዊ ፍትህ እንድሰፍን፣ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ለሀገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊና ተወዳዳሪ ለመሆን ነው፡፡ ይሁንና በክልሉ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ከዚሁ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡
    o በገጠርም ሆነ ከተማ የህዝብ ተስፋን የሚያጨልሙ አፀያፊ ድርጊቶች ስፈፀሙ ማየት የተለመደ ሆኖአል፡፡ በየደረጃው በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ክራይ ሰብሳብዎችና ኮንትሮባንድስቶች፣ ጎሴኛና ጎጠኛ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ግለሰብ አመራር አካላት፣ የአቅምና የአስተሳሰብ ውስንነቶች ያሉባቸው ግለሰቦች የሚፈጥሯቸው ችግሮች መላውን ህዝብ የሚያሳዝንና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሰረቱ በሲዳማ ውስጥ ውስብስብ እና ውዝፍ ችግሮች አሉ፡፡ የእለት ጉርሱን የማያገኝ፣ እንደምንም ብሎ ለቁርስ የሚሆን ምግብ ካገኙ ለምሳና ለእራት ዋስትና የሌላቸው ዜጎች፣ ቤተሰቦች እንዲሁም ወጣቶች በየአከባቢው ብዙ ናቸው፡፡ በየአከባቢው ለልጆቻቸው ቁርስም ሆነ ምሳ ወይም እራት አቅርበው በስነስርዓት የማይመግቡ እናቶች በቁጥር በርካቶች ናቸው፡፡
    በጤናው መስክ ያሉ ችግሮች በጣት የሚቆጠሩ አይደሉም፣ ብዙ ናቸው፡፡ ታምመው የማይታከሙ ወይም በበቂ ደረጃ የህክምና አገልግሎት የማያገኙ፣ በየአከባቢው የጤና ተቋማት እያሉ የተሟላ አገልግሎት ማግኘት ቀርቶ አንጻራዊ አገልግሎት የማያገኙ ዜጎች፣ በተለይም እናቶችና ህጻናት በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ መነሻ በወሊድ ምክንያት እናቶችና ህጻናት ህይወታቸውን የሚያጡ ብዙ ናቸው፡፡ አ/አደሮችም ቢሆኑ ለራሳቸው ታክመው ቤተሰቦቻቸውን ለማሳከም የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም ያለቸው አይደሉም፡፡ በሲዳማ ክልል በርካታ ቤተሰቦች የልማታዊ ሰፍትነት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቤተሰቦች የተወሰኑት ቀጥታ በፔሮል ተተክሎ የሚከፈላቸው ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ የጉልበት ስራ ሰርተው ክፍያ የሚያገኙ ናቸው፡፡
    o በእነዚህ አከባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦች የሴፍትነት ገንዘቡን በአግባቡ አያገኙም፣ ለተረጅ አርሶ አደር ተብሎ የመጣውን የወረዳው አመራሮችና ሙያተኞች ይቀራመታሉ፡፡ አርሶአደሩ ባይተመልካች ነው፡፡
    o በገጠር ወረዳዎች የመጠጥ ዉሃ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም አሳፋሪ ነው፡፡ በገጠር ወረዳ ቅጥር በጉቦና በምልጃ ይፈጸማል፡፡ በሲዳማ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ያለው ሌብነት አሳፋሪና አስነዋሪ ነው፡፡ ለመስማት የሚሰቀጥጥ፣ ለመናገር የሚያስፈራ፣ እና ለማሰብ የሚያዳግት ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ችግሮች በየፈርጃቸው ቀጥሎ ባሉት ክፍሎች የምንዳስስ ሆኖ በዚህኛው ለማየትና ለማሳየት የተፈለገው ቁምነገር ከተበላሸው ከአመራር ስርዓት መነሻነት በህዝቡ ውስጥ ያለውን ህሊናዊና ሁኔታዎች በጣም ከባድ መሆኑን ነው፡፡ በድህነትና በኋላቀርነት ተከቦ በብልሹ አሰራር መነሻነት የሚማቅቅ ህዝብ የሚያሳዝን ነው፡፡ ስለሆነም ዝርዝር ጉዳዮችን ከዚህ በታች ባሉት ክፍሎች እንመለከታለን፡፡
  5. የችግሮቹ ሁኔታ በየዘርፉ፤
    የየዘርፉ ችግሮችን ለማሳየት የተሞከረው በዋናነት ከአመራር ስርዓት አንጻር ነው፡፡ አሁን ያለው አመራር ቲም በክልሉ ያሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና መሰል ችግሮችን መፍታት የማይችል መሆኑን ከላይ ባሉት ክፍሎች ውቅያኖስን በጭልፋ የመሞከርን ያህል ሞክረን አስቀምጠናል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በታች ያሉ የየዘርፎቹ ችግሮችም ቢሆን አጠር ባለ መልኩ ተቀምጧል እንጅ የተሟላ አይደለም፡፡ በመሆኑም ክቡራንና ክቡራት ይህንን ሰነድ የሚታገኙ ወገኖቻችን ካቀረብነው ጭብጥ ተነስታችሁ የራሳችሁን ግምት እንደምትወስዱ እምነታችን የፀና ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናት የምደረግ ከሆነም የትኛውንም አካል ያለአንዳች ወጭ/ክፍያ ለማገዝ ዝግጁዎች መሆናችንን በታላቅ ትህትና ለማሳወቅ እንሻለን፡፡
    5.1 በግብርና/እንስሳት፣ በትምህርት እና ጤና መስኮች ያሉ ችግሮች
    5.1.1 በግብርና እና በእንስሳት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች
    ግብርና እና የእንስሳት ዘርፍ ስራዎቻችን የኢኮኖሚያችን መሰረት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ ያለ ህዝባችን ኑሮውን መሰረት ያደረገው በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት ይህንን ዘርፍ በማዘመን የህዝቡን ኑሮ ለመቀየር፣ በግብርና የተያዘው የመሪነት ድርሻ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲተካ እና ይህንኑ ራዕይ ለማሳካት ዓይነተኛ ሚና ያላቸው ስትራቴጂዎች መቅረጽን ጨምሮ የፖሊስ ማሻሻያዎችም በየወቅቱ እንደሚደረጉ ከሁላችን ልቦና የተሰወረ አይደለም፡፡ አርሶ አደሮች በልማት ጣቢያ ሰራተኞች ታግዘው ዘመናዊ የአስተራረስ ስነ-ዘዴ እንድከተሉ እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ገበያ መር የአስተራረስ ዘይቤ በመከተል ከራሳቸው አልፈው ለአከባቢና ለማዕከላዊ ገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርቱ ማስቻል የመንግስታችን ቁልፍ አቅጣጫ እንደሆነ ልቦናችን ያውቃል፡፡
    ይሁንና በሲዳማ ክልል ያለው የግብርናም ምርትና ምርታማነት ሁኔታ በየሰብል ዓይነቱ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማለትም ምርጥ ዘርና፣ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና አጠቃቀም የውጤታማነት ችግሮች ያሉበት መሆኑን በየወረዳው ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ በተመሳሳይ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራዎች በውጤታማነት እየተፈጸመ ባለመሆኑ የሀገር ሰብም ሆነ የውጭ ዝርያ ያላቸው ከብቶች የወቴትና የስጋ ምርታቸው ከዜጎች ፍላጎት ጋር የተመጣጠ አይደለም፡፡ ይህ ዘርፍ ለወጣቶች ስራ እድል ከመፍጠር አልፎ ለአከባቢና ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አዎንታዊ ድርሻውን በትክክል እንድወጣ እየተሰራ አይደለም፡፡ ሁለቱም ዘርፎች የኤክስቴንሽን አገልግሎትና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ክትትልና ሙያዊ ድጋፍ ትኩረት የተነፈገው ነው፡፡
    ከግብርና ልማት ስራችን አንጻር በክልሉ ያለው ስነምህዳር/አግሮኢኮሎጅ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- ሜልጋ በአብዘኛው፣ የጎርቼ ወረዳ በከፍል፣ አብዘኛው የአርቤጎና ወረዳ፣ የቡርሳ ወረዳ በአብዘኛው፣ የሻፋሞ ወረዳ በሙሉ፣ የጤጢቻ ወረዳ በሙሉ፣ የሁላ ወረዳ በአብዘኛው፣ የጪሮኔ ወረዳ በአብዘኛው፣ ቦና ዙሪያ ወረዳ በከፍል፣ የቡራ ወረዳ በሙሉ፣ የበንሳ ወረዳ በከፍል ፣ የዳኤላ ወረዳ በሙሉ እና የወንሾ ወረዳ በከፍል የደጋማ ዓየር ንብረት ያላቸው ወረዳዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ወረዳዎችም የወይና ደጋ አየር ንብረት ያላቸውም አከባቢዎች አሉ፡፡ የተቀሩት፣ ለምሳሌ፡- አለታ ወንዶ በአብዘኛው፣ ሎካ አባያ በሙሉ፣ ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በሙሉ፣ ዳሌ በሙሉ፣ ዳራ-ኦትልቾ በአብዘኛው፣ አለታ ጩኮ በሙሉ፣ የቢላቴ ዙሪያ ወረዳ በሙሉ፣ ጫቤ-ጋንቤሊቱ በሙሉ እና የሆኮ ወረዳዎች በቆላማ እና በወይና ደጋማ አግሮ-ኢኮሎጂ /ስነምህዳር ጠባይ የሚመደቡ ወረዳዎች ናቸው፡፡
    በክልላችን የአርሶ አደሮችን ኑሮ ለመቀየር እና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ተጨማሪ አቅም ለመሆን ስነምህዳርን መሰረት በማድረግ መስራት እንደሚገባ ከላይ ለማሳቀመጥ ተሞክሯል፡፡ ለምሳሌ፡- የቡና ልማት፣ የእንስሳት ልማት( ማድለብ፣ ማሞከት፣ የወተት ልማት…)፣ በሰብል ልማት እና በሌሎች ሰብል አይነቶች የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል፣ይገባልም፡፡ በዚህም የህዝቡን ኑሮ ከማሻሻል አልፎ የሀገራችንን ኢኮኖሚ የመደጎም አቅምንም መፍጠር ይቻላል፡፡
    o ለምሳሌ፡- በወተት ልማት ስራ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ማስገባት ከተቻለ ከፍተኛ እድገት በቤተሰብ ደረጃ ለማምጣት የሚያስችል ፓኬጅ በእጃችን አለ፡፡ የወተት ላሞች አርብና አምራች ማህበራትን በስፋት ማደራጀት፣ የተመረተውን ወተት ተረክበው ለተጠቃሚዎች ወይም ለሚያቀነባብሩ ተቋማት የሚያደርሱ ማህበራትን በስፋት ማደራጀት እና ቀጥታ ምርቱን ተረክበው የሚያቀነባብሩ ማህበራትን በማደራጀት የፋይናንስና የሊዝ ማሽነሪዎች ድጋፊ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ዘርፍ አንድም ከፍተኛ የሆነ የገበያ ጉድለት ያለበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ስራዉም ምቹ፣ የብዙ ወጣቶች ችግር የሚፈታ እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አይነተኛ ሚና የሚጫወት እንደሆነ ብታመንም በመዋቅሩ ዳተኝነት አልተሰራበትም፡፡
    o ሌላው በቡና ልማት ስራ ላይ የሚታይ ዳተኝነትና ሌብነት ነው፡፡ በክልላችን የቡና ልማት ስራ በሚፈለገው መልኩ የምርጥ ዘር እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያለው አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት የደጋ ስነምህዳርን ጨምሮ አብዘኛው የሲዳማ አከባቢዎች ለቡና ልማት ምቹ ናቸው፡፡ ከክልሉ ፊት አመራር ጀምሮ በየደረጃ ያለው የዘርፉ ባለሙያዎች በቢሮ ተቀምጠው ያለአንዳች ጥናት የእሸት ቡና መፈልፌያ ፈቃድ በማደል ክራይ ከመሰብሰብ ወጭ ተቋማዊ የሆነ ክትትልና ግምገማ ለዚህ ዘርፍ አይደረግም፡፡
    የሲዳማ ህዝብን ትራንስፎርም ለማድረግ አግሮ-ኢኮሎጂውን ማዕከል ያደረገ የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ልማት ስራዎችን መስራት ይቻላል፣ይገባልም፡፡ እንደየአከባቢው ሁኔታ እስፔሻላይዝ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉን፡፡ ይሁንና ከክልል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ በየደረጃ ያለው የቢሮው መዋቅር በሲዳማ ውስጥ ያለውን ፀጋ/ potential በውል ለይቶና ገምግሞ፣ ለዚህ ደረጃ የሚመጥን መሪ እቅድ/strategic plan አዘጋጅቶ የሚሰራ ኃይል ባለመኖሩ፣ የሲዳማ ህዝብ በድህነት እሽክርክሪት ውስጥ ይዳክራል፡፡
    o NB፡- በሼልፍ ላይ ያለውን የ10 ዓመት እቅድ ዘንግተን አይደለም፡፡
    በሲዳማ ክልል የግብርና እና የእንስሳት ምርት እድገትን በእያንዳንዱ ከብት ዝርያ ወይም ሰብል ዓይነት የምርታማነት ምጣኔ ወይም የምርታማነት ሁኔታ በምርት ትመና ዘዴ እየተለየ ካልሄደ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ከግብርና ስራዎች አኳያ በየወረዳው፣ በተለይም በወይና ደጋ እና በቆላማ አከባቢዎች ከሚመረቱ ሰብሎች አንዱ የአገዳ ሰብል የሆነው የበቆሎ ምርት ነው፡፡ በደጋማ ክፍል በአብዘኛው የሚመረተው ስንዴ ነው፡፡ የእነዚህ ሰብሎች የምርታማነት ሁኔታቸው ወይም ደረጃቸው ምን እንደሆነ በግምት ከሚነገረው ውጭ በውል አይታወቅም፡፡ በሁሉም አከባቢዎች፣ ሁሉንም የሰብል ዓይነቶች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የምርት እድገት እየታየበት አይደለም፡፡ የየሰብሎች የምርታማነት ሁኔታቸው ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ ለምን? ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ጥቅቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
     ቁልፉ ችግር የሚሆነው የአመራር ስርዓት ደካማ እንደሆነ ቢታመንም ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም አሉበት፡፡
     በየደረጃ ያለው የግብርና መዋቅር በአርሶ አደሮች አስተሳሰብ ላይ የሰራው ስራ ደካማ መሆን፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ወቅታዊነትና ተገብነት ችግሮች (ለስነምህዳር የሚመጥን ግብዓት አለማቅረብ)፤
     በየአከባቢው ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ያለው መሬት ከቤተሰብ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ አለመሆን፣ የአፈር ለምነት ችግሮች፣ የቤተሰብ ጉልበት አጠቃቀም ችግሮች፤
     የግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓትን በመከተል የግብርና ባለሙያዎች/SMS ለአርሶ አደሮች የሚሰጡት ሙያዊ ድጋፍና ምክረ አገልግሎት አለመኖር፣ ለዚህ ተግባር የተመደቡ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ዘርፉን ቀይረው ከየቀበሌው በመነቀላቸው እና ያሉትም ቢሆን አርሶ አደሮችን በአግባቡ እየደገፉት አለመሆኑ፤
    ሌላኛው በዘርፉ የሚታየው ችግር የአመራር ስምሪትና ስርዓት የተዛነፈ መሆኑ ነው፡፡ ከቢሮ ኃላፊዎች ጀምሮ በየደረጃ ያለው የአመራር ቲም የተራድኦ በጀቶችን እንድቀራመት ታስቦ የመደበ አካል ይመስላል፡፡ በዝምድና፣ በጋብቻ፣ በጓደኝነት በወዘተ መነጽር ታይተው የተመደቡ በመሆናቸው የህዝቡ ችግር አይታያቸውም፡፡
    በመሆኑም በሲዳማ ክልል በየአከባቢው ያለው ነባራዊ ሁኔታ በእጅጉ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አርሶ አደሮቻችን ምርታማ እየሆኑ አይደሉም፣ በየአከባቢው ድህነት በጣም ተስፋፍቷል፣ በየድግስ ቦታዎች እየተገኘ ለታዳሚዎች የተሰናዳውን ምግብ በኃይልና በጉልበት ነጥቆ ለመብላት አሰፍስፎ የሚመጣ ወጣት፣ በየለቅሶ ቤት እየመጡ ኮሮጆ ይዘው ምግብ የሚለምኑ እናቶቸና ህጻናቶች ጉዳይ የማይገደው እና የሀዋሳ ከተማ ጎዳናዎችን ጨምሮ በየከተሞች እየዞሩ የሚለምኑ ወገኖች ጉዳይ ምንም የማይመስለው የግብርና መዋቅር ነው ያለን፡፡
    በገጠር በትምህርትና በግብርና ስራ ውጤታማ ያልሆነ ዜጋ ሁሉ ወደ ከተማ ይፈልሳል፡፡ ጤናማ ያልሆነ የሰዎች ፍልሰት ያለ መሆኑንም መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡ የገጠር እና የከተማ ትስስር በተቃርኖ የተሞላ እየሆነ ነው፡፡ ገጠር፣ የከተማ ህዝብን በተገቢው እየደገፈ ካልሄደ፣ ወጣቶች በገጠር ቆይተው እና ከወላጆቻቸው ጎን ሆነው ባላቸው ማሳ ልክ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን አምርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ደጉመው የገበያ ችግሮችንም እየፈቱ አይደሉም፡፡ በመሆኑም በገጠር የጉልበት አጠቃቀም ችግር ብቻ ሳይሆን ወላጆችን አስጨንቀው የምመግቡ እና የሚለብሱ ጡረተኛ የሆኑ ወጣቶች በየአከባቢው ብዙ ናቸው፡፡ ስለሆነም የግብርና እና የእንስሳት ምርትና ምርታማነት እድገት አለመኖር ሁሉንአቀፍ ችግሮቻችንን እንዳንፈታ እያደረገን ነው፡፡
    የልማታዊ ሴፍትነት ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ መደበኛ የግብርና ልማት ስራዎችን በመደገፍ በየአከባቢው ያሉ አርሶ አደሮች በዚህ ፕሮግራም ታግዘው ጊዜያዊ ችግሮቻቸውን ፈትተው በዘላቂነት የቤተሰባቸውን የመመገብ ስርዓትን ማሻሻል እና መጻዕ የኑሮ ሁኔታቸውን መገንባት እንደሆነ አያከራክርም፡፡ በክልሉ ውስጥ ካሉ ገጠር ወረዳዎች መካከል በ20 ገጠር ወረዳዎች ያሉ የድሃ ድሃ የተባሉ አርሶ አደር ቤተሰቦች በዚህ ፕሮግራም ይደገፋሉ፡፡
    o በየወረዳው ከተጠቃሚ አርሶ አደር ምልመላ ጀምሮ የጎላ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የችግሮቹ መልክ ብዙ ቢሆኑም ዋነኞቹ ግን የፍትሃዊነት እና የክራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ እንደሆነ ማስመር ያስፈልጋል፡፡
    o የቀበሌ አመራር በተጠቃሚ አርሶ አደር ምትክ የራሱን ስም ያስገባል፣ የቤተሰቡንና የጓደኛውን ስም ያስገባል፣ መልምሎ በማስገባት እና ክፍያ በመፈፀም ሂገት ውስጥ ጉቦ ይወስዳሉ፣ ሌሎች ጉድፎችንም ይፈጽማል፡፡
    o በፔሮል ተተክሎላቸው የሚሰውዱትን ጨምሮ በጉልበት ስራ ተሰማርተው የሚሰሩ ሰዎች የላባቸውን ምንዳ በተገቢው እንደማያገኙ በተለያየ ጊዜ ያደረግነው ክትትልና መረጃ ያስረዳል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በየደረጃው በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ሆነ አመራሮች ከተረጅዎች ተለይተው የሚታዩ አይደሉም፡፡
     በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር በዚህ መስክ ተመልምለው ዕለታዊ ችግራቸውን እየፈቱ፣ በዘላቂነት የራሳቸውን አቅም እንዲያዳብሩ ታስቦ የተዘረጋው የልማታዊ ሴፍትነት ፕሮግራም አርሶ አደሮች የጥገኝነት አመለካከት እንድያዳብሩ እያደረገ ነው፡፡ በተደራጀ መልኩ ተጠቃሚዎችን የማስመረቅ ስርዓት የለም፡፡
     በመሆኑም ይህንን ጊዜያዊ ድጎማ ተጠቅሜ በዘላቂነት የራሴንና የቤተሰበን ህይወት እቀይራለሁ የሚለውን እምነት ከመያዝ ይልቅ በአቋራጭ እንዴት ሆኜ በዚህ ልሰንብት የሚል ጥገኛ አስተሳሰብ መያዝ ይታያል፡፡
     ቢሮውም ሆነ የየደረጃው መዋቅር እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰቦችን በድጋፍና ክትትል ቀርፎ አርሶ አደሮችን ደግፎ የማሸጋገር፣ የማስመረቅ እና ሌሎች አዳዲስ ተጠቃሚዎችን በፍትሃዊነት እየመለመለ ልማታዊነት እንድጎለብት ከመስራት ይልቅ አሉታዊ አስተሳሰብ ስፍራውን እንዲይዝ የሚያበረታታ ይመስላል፡፡
    በድምሩ፣ የሲዳማ ክልል የግብርና እና እንስሳት መዋቅሮች በብዙ መመዘኛዎች ስገመገም ቆሞ-ቀሮች እንደሆኑ ከላይ የተጠቃቀሱ አብነቶች አመላካቾች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ዘርፎች አኳያ በክልሉ ያሉ ችግሮች የአንድ ወቅት ባይሆኑም እንደአመራር ያሉ ማነቆዎችን በአግባቡ ገምግሞና አቅዶ መፍታት ይቻላል፡፡ በክልሉ ያሉ አርሶ አደሮች የመሬት አያያዛቸው በአማካይ ከአንድ ሄክታር በታች የሆነ እና ከፍተኛ ጥግግት ያለበት አከባቢ በመሆኑ ለዚህ ደረጃ የሚመጥን ፖለቲካዊ አመራር የሚሰጥ፣ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በሚያደርጉ አካላት ላይ ሪፎርም ካልተደረገ፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና አጠቃቀም ችግሮችን ገምግሞ የሚያስተካል አካላትን በየደረጃው መመደብ ካልተቻለ የሲዳማ ህዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በድህነት አለንጋ እየተገረፈ መዝለቁ የግድ ይሆናል፡፡ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል፤ ነገር ግን ለዚህ የሚመጥን የአስተዳደር ስርዓት በሲዳማ ውስጥ መገንባት ካልተቻለ ራዕዩ የህልም እንጀራ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ይሆናል፡፡
    5.1.2 ትምህርት እና ችግሮቹ
    በሲዳማ ክልል የትምህርት ስርዓት በሚመለከት በየትምህርት እርከኑ የሚስተዋሉ ችግሮችን፣ የችግሮቹ ባለቤቶችን እና የመፍትሄ አማራጮችን ለመጠቀም የሚያዳግት ነገር የለም፡፡ በሲዳማ ክልል ካሉ ተቋማት ውስጥ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ ውድቀት የገጠመውና እየገጠመው ያለው ይህ ዘርፍ ነው፡፡
    በእኛ እምነት፣ የተማሪዎች ወጤታማነት የሚለካው፣ የትምህርት ጥራት ደረጃ የሚወሰነው በዋናነት በዓመቱ መጨረሻ ላይ የተማሪዎች ውጤት እና ስነምግባር ላይ የሚታየው ውጤት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ባንገባም፤ የተማሪ ክፍል ጥምርታ፣ የተማሪ መምህራን ጥምርታ፣ የተማሪ መቀመጫ ማሟላት፣ የተማሪ መጽሃፍት ጥምርታ እና የወላጅ-መምህር መስተጋብርና እንቅስቃሴ ለተማሪዎች ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንዳለው ሁላችንም እናምናለን፡፡ በመሆኑም በዚህ መስክ በየትምህርት እርከኑ በመንግስት እና በህ/ሰቡ ተሳትፎ የተሰሩ ስራዎች ያሉ ቢሆንም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም፡፡ በሲዳማ ክልል የትምህርት ስራ ውዝፍ ችግሮች ያሉበት ሆኖ፣ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መዋቅር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተዘጋጀ አይደለም፡፡
    በዘርፉ ያሉ ችግሮች ምን ምን ናቸው? ውቅያኖስን በጭልፋ የመጭለፍ ያህል እንደሚከተለው ለማስቀመጥ ጥረት ተደርጓል፡፡
    o በገጠርቱ ሲዳማ አከባቢዎች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ባለመኖሩ ህጻናት አስቀድመው ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት እድል የሌላቸው መሆኑ፤ ከዚህም የተነሳ 1ኛ ክፍልን ያለአንዳንች ዝግጅት ስለሚገቡ ትምህርት አቀባበላቸው ሁኔታና የዉጤታማነታቸው ልክ ጉድለት ያለበት መሆኑ፤
    o በሁሉም ቀበሌያት ቢያንስ 2 ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ት/ቤቶች ከ1ኛ እስከ 8ኛ ደረጃ ያሉ ሲሆን የተማሪ ክፍል እና መጽሃፍት ጥምርታቸው ችግር ያለበት መሆኑ፤ በዚህ ደረጃ ያሉ ችግሮችን የሚፈታ አመራር በየደረጃው የተመደበ ቢሆንም ችግሮችን መፍታት እየቻለ አይደለም፡፡
    o ከስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ሂደት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ሁላችንም እንደሚናውቀው የትምህርት ይዘቱ ተቀይሯል፡፡ ማለትም ከ1-6 የተፈጥሮ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ መሆን ፤ከ7-8 ባዮሎጅ፣ ከሚስትሪ እና ፊዚክስን አጣምሮ የያዘ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ተፈጠረ?
     በዚህ ቅኝት ለመምህራን ስልጠና ሰጥቶ ያለማሰማራት፣ ከዚህ የተነሳ መምህሩ በሁሉም የትምህርት ዓይነት እኩል ችሎታ ስለማይኖረው በቂ የሆነ እውቀትን ለተማሪ ከማስጨበጥ አንጻር ችግር ያጋጠመው መሆኑ፤
     በአዲስ መልክ የተዘጋጁ ማጽሃፍትን በተማሪ ልክ ተመጣጥነው ባለመቅረባቸው በመማር ማርተማር ሂደት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ በዚህም ወረዳዎች አባዝተው ለት/ት ቤቶች እንዲያደርሱ ለሁሉም መዋቅር ሰነዱን በሶፊት ኮቲ የተሰጠ ቢሆንም ፣ ወረዳዎች ደግሞ የበጀት ችግር ያለባቸው በመሆኑ ለተማሪዎች የሚሆን መጽሃፍት ማቅረብ አልተቻለም፡፡
     በዚህ ሂደት የወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ለመምህሩ ማስተማሪያ የሚሆኑ መጽሃፍት ብቻ ያቀረበ መሆኑ እና ይህም ስርዓተ ትምህርቱ የተቃኘበትን ቅኝት የሚጣረዝ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ በመሆኑም “ተማር ተኮር” የማስተማር ዘዴ ያልተከተለ የማስተማር ተፈጻሚ እየሆነ ይገኛል፡፡ በዚህም ብዙ ተግባራት ተማሪው ከመጽሃፍት እያዬ የምማርባቸው ሆነው እያሉ ከመምህሩ ገለጻ ብቻ እንዳንድ ነገሮችን እየለቃቀመ የሚውል ሆኖአል፡፡
    o ሌላኛው ችግር የክልሉ ትምህርተ ቢሮ ኃላፊ ለትምህርት ስራ ትኩረት የማይሰጥ መሆኑ ነው፡፡ አመራሩ፣ የምክትል ርዕሰ መስተዳደሪ ኃላፊነት በተደራቢነት የተሰጣቸው በመሆኑ የቢሮውን ስራ በተገቢው እየገመገመ አይመራም፡፡ በመሆኑም የክልሉ የትምህርት ስራ በተገቢው እየተደገፈ ያለመሆን፣ ለዚህም ከስር ያሉ ባለሙያዎች ትምህርት ቤቶችንና ወረዳዎችን ለመደገፍ በኃላፊ አስገምግመው ወደታች ለማውረድ መቸገር፤
    o ከመምህራን ልማት መርሃ ግብር አንጻር ያሉ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ለ2ኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች በቂ የሰው ኃይል ባለመቀጠሩ እና ከ1ኛ ደረጃ ብቻ የክረምት ትምህርት ጀምሯል/ጀምራለች እየተባለ ክፍተቱን ለመሸፈን የሚሰራ መሆኑ፤
    • ተማሪ በበቂ ያለመማር/አለማስተማር
    • መምህሩም ከአቅም በላይ የሆነ ሸክም ይዞ መቸገር(2ኛ ድግሪ የምጠይቀውን ቦታ በዲፕሎማ ማስተማር)
    o ትምህርት በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሰጥ የኢፌዲሪ መንግስት ብዙ ዋጋ ከፍሎ ተግባራዊ እንዲሆን ያለውን የፕላዝማ ቴሌቪዥን የትምህርት አሰጣጠ ሂደትን ክልላችን በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው በማለትና በውሸት ሪፖርት ትምህርት ሚኒስቴርን በማሳሳት የሀገርቱን የትምህርት ስርዐት ትግበራ ሂደትን ከማዛባት ባለፈ ፣ በህጻናት ህይወት ላይ ቁማር የሚጫወት አመራር ኃይል መሆኑን ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በአጽንኦት እንዲረዳልን እንሻለን፡፡
    o ሌላኛው ጉዳይ የርዕሰ መምህራንና የሱፐርቫይዘሮች የደረጃ ክፍያ መቋረጡ የፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የመምህራን፣ የርዕሰ መምህራን እና የሱፐርቫይዘሮች ወርሃዊ ደመወዝ እኩል የመሆን እድል ገጥሞታል፡፡ ይህም በመሆኑ፣ በአብዘኛው ት/ት ቤቶች ያሉ ርዕሰ መምህራን ለምን ተቸግረ ቀኑን ሙሉ አስተምራለሁ፣ ምን አስጨነቀኝ፣ የማገኘው ደመወዝ ከመምህሩ እኩል እስከሆነ ድረስ ትንፋሸን እየሰበሰብኩ እሰራለሁ በማለት ፣ በትምህርት ስራ ላይ ቸልተኛ አቋም የመያዝ ነገር ይታያል፡፡(ይህ ችግር የክልላችን ችግር ብቻ መሆኑ)፤
    በትምህርት ዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ሌብነት እና የመልካም አስተዳደር እጦት ተጠቃሾች ናቸው። በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት የስልጠና ማሽነሪዎች ተሰርቋል። ማሽነሪዎቹ የተሰረቁበት መንገድ ተቋማዊ አድርገን ለመገምገም እድል ባናገኝም ፣ እንደ አንድ ተራ ዜጋ ግን ግምታችንን ማስቀመጥ እንችላለን። ግምት ብቻ ሳይሆን ለእውነት የተጠጋ መረጃም አለን። የስልጠና ማሽነሪዎችን በተባባሪነት ያሰረቀው እና ሽጦ የተከፋፈለው አመራሩ ነው። ዝርዝር መረጃው በምርመራ እንደሚገኝ እምነታችን የፀና ነው።
    ባጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮች ውዝፍ ቢሆኑም በቁርጠኝነት ከተሰራ መፍታት ይቻላል፡፡ በየአከባቢው ያሉ ችግሮችን በተስተካከለ በአመራር አቅምና ስርዓት መፍታት የሚቻል ቢሆንም የሚፈታ አካል ግን የለም፡፡ የቢሮው አመራር ለትምህርት ጥራት ፣ ለተማሪዎች ስነምግባር መሻሻል የመጡ የፕሮጀክት በጀቶችን እየተቀራመተ በሀዋሳ ከተማ መሬት የሚገዛና የሚቸረችር ነው እንጅ የስራው ባለቤት አይደለም፡፡ ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡
    5.1.3 የጤናው ዘርፍ እና ችግሮቹ
    በሲዳማ ክልል በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮች ዘርፈብዙ ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች አንድ በአንድ መዘርዘር ከባድ ይሆናል፡፡ ይሁንና ለግንዛቤ እንድረዱ የተወሰኑ ችግሮችን ለመጠቆም ያህል የሚከተሉትን አስቀምጠናል፡፡
    በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ጨምሮ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ተገንብተዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት ውስጣዊ የብቃት ችግር ያለባቸው መሆናቸውን ተጨባጭ እንቅስቃሴያቸው ያሳያሉ፡፡ መሰረታዊ ችግሮቻቸው ምን ምን ናቸው? የጤና ተቋማት ቁልፍ ችግሮች የአመራር ትኩረት አለማግኘት ስሆን ከዚሁ መነሻ በየተቋሙ የመልካም አስተዳደር እጦት(ባለሙያዎች የፈጠሩት፣ አስተዳደር አካል የፈጠረው) ፣ ክራይ ሰብሳቢነት (በመድሃኒትና በፋይናንስ) እና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
    የህ/ሰቡን ጤና ለማሻሻል ታስቦ የተቀረፁና ላለፉት አስርት ዓመታት በየደረጃው ስተገበር የቆዩ በሽታ የመከላከል ስራዎች በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡
     በየአከባቢው የተገነቡ አብዘኛው ጤና ኬላዎች ተዘግተው የሚውሉና እናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሚፈለገው መጠንና ሁኔታ እያገኙ አለመሆን፤
     የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በአብዘኛው ሙያቸውን ቀይረው ወደ ሌላ ተቋም የኮበሌሉ ስሆን የተቀሩትም ሆን የህ/ሰቡን ህይወት የምቀይር ስራ አለመስራት፤
     ህጻናት በእድሜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን ክትባት እያገኙ አለመሆን፤
     በየወረዳው በምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት ተገቢው ልየታ ባለመካሄዱና ተመጣጣኝ ባለመሰጠቱ ለከፋ ምግብ እጥረትና ሞት እየተዳረጉ መሆኑ፤
     ህብረተሰቡ፣ በተለይም በቆላማ አከባቢዎች እንደ እነ ሀዋሳ ዙሪያ ፣ ቢላቴ ዙሪያ፣ ሎካ አባያ፣ ዳራራ፣ ይርጋሌ፣ ሌኩ በከፍል ፣ ጩኮ እና ሆኮ ወረዳዎች ያሉ ህ/ሰብ ወባን ጨምሮ የተላላፍ በሽታዎች ተጠቅ ሆኖአል፤
    በሌላ መልኩ የጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የግብዓት አቅርቦት እና የአመራር ሁኔታቸው በችግሮች የተወጠረ ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ የሀዋሳ ሪፌራል ሆስፖታልን ጨምሮ በርከት ያሉ መካከለኛና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስቲታሎች አሉ፡፡ በተመሳሳይ በ36 ገጠር ወረዳዎች በአማካይ 4-5 ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ይቅርና በግማሽ አቅማቸው እንኳን ለህ/ሰቡ አገልግሎት መስጠት ከቻሉ በጣም በቂ ነው፡፡ ነገር ግን እየሆነ ያለው በጣም አሳዛኝና ዘግናኝ ነው፡፡
     በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የግብዓት እጥረት ያለባቸው መሆኑ (የመድሃኒት፣ የላቦራቶሪ ሪኤጀንት፣ ህክምና መገልገያ መሳሪያዎች)፤
     ለማዋለድ አገልግሎት እንኳን የሚሆን ግላቪ በየሆስፒታሉ ባለመኖሩ ሀኪሞች በፔስታል ለማዋለድ የሚገደዱበት ሁኔታ መፈጠሩ እና ይህንን ችግር አይቶ የሚፈታ የስራ አመራር ቦርድም ሆነ ማነጅሜንት በየአከባቢው አለመኖር ችግሩን መሪር የሚያደርገው መሆኑ፤
     በየተቋሙ መሰረታዊ የድንገተኛ መድሃኒቶች እጥረት መኖር፣
     ለመድሃኒትና ለህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዥ የሚውል በጀት አለመያዝ፤
     በየተቋሙ ተኝቶ ታካሚዎች የምግብ አቅርቦት አለመኖር፤
     በየተቋሙ የእናቶችና የህጻናት ሞት መበራከት( በባለሙያና በአመራር እንዝላልነት)
     አንቡላንሶች ለእናቶችና ለህጻናት ጤና አገልግሎት ዉጭ መሆን(በየደረጃ ያለው የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች ለማመላለስ የሚውል መሆኑ)፤ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ አንቡላንሶች ደግሞ በበቂ ሁኔታ ጥገና ስለማይደረግላቸው በየቦታው ወድቀው የቀሩ መሆናቸው፤ የአንዳንድ ወረዳ አንቡላንሶች ደግሞ በጣም በሚያሳዝን መልኩ የትራንስፖርት መኪና እስክመስሉ በመናኸሪያ ጀርባ ቆመው መንገደኞችን የሚጭኑ መሆኑ፤
     በተያያዘ ለወረዳ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ስኬታማነት አይነተኛ ሚና እንድጫወቱ ታስቦ የመጡ ተሽከርካሪዎች ከዓላማ ውጭ ለሌላ ዓላማ እየዋሉ መሆናቸው፤
     የጤና መድህን አባልነት ምጣኔ በጣም ዝቅተኛ መሆኑና ህ/ሰቡ የተወደደውን/ከፍ ያለውን የህክምና ክፍያ መክፈል ባለመቻላቸው በተለያየ ህመምና ሞት ሰሌባ የሚሆኑ መሆኑ፤
    በዚህ ዘርፍ ሌላኛው፣ ምናልባትም ለተቋሙ ውድቀት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ያለው በየደረጃ ያለው የዘርፉ አመራር በግለኞችና በሌባ ግለሰቦች የታጠረ መሆኑ ነው፡፡ በሲዳማ ክልል ያሉ የጤና ተቋማት ለሌብነት የተመቹ ናቸው፡፡ በየደረጃው መልካም ስነምግባርና አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች መኖራቸውን ያህል በእጅጉ ህ/ሰቡን በተለያየ መንገድ የሚጎዱ አመራሮችና ሙያተኞች አሉ፡፡ በመሆኑም በአብዘኛው ጤና ተቋም ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች( ሀኪሞች፣ ነርሶች፣ ወዘተ) በተናጠልና በጋራ የሚሰርቁ፣ የሚያሰርቁ እና በህ/ሰቡ ላይ በደል የሚፈጽሙ ናቸው፡፡
     ከመድሃኒት እና ህክምና መሳሪያዎች ግዥ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም ሌብነት በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ የመንግስት መድሃኒት አቅርቦት ድርጅት ከግል መድሃኒት ቸርቻርዎች ጋር በመመሳጠር፣ የመንግስት ሆስፒታሎች የሚያቀርቡአቸውን የግዥ ፍላጎቶችን ካላቸው ስቶክ/stock ጋር በመሸት መረጃ በማመሳከር እና ያላቸውን መድሃኒት በመደበቅ ይህንን፣ እነዚህን ከሌላ ቦታ ግዙ፣ ለጊዜው የለንም፣ ያለን ይህ ብቻ ነው በማለት በዚህ መኃል የሚፈጽሙት ሌብነትና ውንብድና ከፍተኛ መሆኑ፤
     የጤና ድርጅቶች የውስጥ ገቢ አጠቃቀም ከመንግስት ደንብና መመሪያ ውጭ መሆኑ እና በየደረጃ ያሉ ካድሬዎች፣ ስራ አስኪያጆች እንዲሁም የስራ አመራር ቦርድ ኃላፊዎች የሚቀራመቱበት መሆኑ፤ በኦዲት የማይደገፉ ጫካዎች ናቸው፡፡
     በተለያዩ ፕሮጀክቶች ስም የሚመጡ በጀቶች ለተያዘው ዓላማ የማይውሉ መሆናቸው ( ለአክትቪስቶችና ዴላላዎች የሚከፈል በጀት ነው)፤
     በሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ግብ ውስጥ ሊሰራ የታቀደውን የአደራሽ ግንባታ የቢሮ ኃላፊዋ ባለቤት ከአሰራር ውጭ እንዲገነባ የተሰጠው እድል በክራይ ሰብሳብነት ስለት ነው፡፡
     በተለያዩ ጤና ድርጅቶች ደረጃ ለምሳሌ፡- የሀኪሞች ማደሪያ፣ የማስፋፊያ ግንባታዎች፣ የወባ መድሃኒት ማከማቻ መጋዝኖች፣ የቀዶ ጥገና ብሎኮች ወዘተ ቅድመ ክፍያ ተከፍሎ ቆሞ የቀሩ ብዙ ናቸው፤
     የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች የማይከፈልበት መሆኑ፣ በየጤና ድርጅቶች መልካም አስተዳደር ችግሮች ያሉባቸው ባለሙያዎች ብዙ መሆናቸው እና ከዚህም የተነሳ የባለሙያዎች ተነሳሽነት ችግር ያለበት መሆን፤
     ከግል ጤና ድርጅት ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም ሌብነት፤
     ለእናቶችና ለህጻናት ጤና መሻሻል እንዲሁም በሽታዎችን ለመከላከል የተላኩ በጀቶች በዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በጋራ ጥምረት የሚበላ መሆኑ፤
    በአጠቃላይ ጤናው ሴክተር መደበኛም ይሁን በፕሮጀክትና ፕሮግራሞች ታግዘው የሚሰሩ ስራዎች ከታሰበው በላይ እንዳይሄድ ቀፍድደው የያዙ ችግሮች በዋናነት ከቢሮ ጀምሮ የጤና ድርጅቶች አመራሮች ደካሞችና በሌብነት አዕምሮ ውስጥ ሆነው የሚመሩ መሆናቸው ነው፡፡ ሌላውና ትልቁ ችግር ከቢሮ ማነጅሜንት ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር አካላት ስራዎቹን ተቋማዊ አድርገው የማይገመግሙና በግል ጉዳዮች የተጠመዱ፤ በላይ ኃላፊዎቻቸውም ቢሆኑ የሚደርሳቸውን ከወሰዱ ወዲያ በየጤና ድርጅቶች የሚፈፀሙ በደሎችን፣ እንግሊቶችን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማየት መነጽር የላቸውም፡፡
    5.2 የወጣቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች
    5.2.1 የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና የወላጆች ሰቆቃ
    የሲዳማ ህዝብ በቁጥር ወደ 8.8 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በክልሉ ዉስጥ ካለዉ ህዝብ ቁጥር አንፃር የወጣቶች ድርሻ (በግርድፉ) ከ60-70% እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ይህ ሀይል በገጠርና በከተማ የሚኖር ሲሆን በትምህርት ዝግጅት፣ በኢኮኖሚ መስክ ተጠቃሚነት እና በንቃተ ህሊናቸው ደረጃ ስገመገም ደግሞ በተለያየ ደረጃ የሚቀመጥ እንደሆነም እሙን ነው፡፡
    በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዉስጥ (በቆላ በደጋ) ከፍተኛ የሆነ ድህነትና ኃላቀርነት የከበባቸው የህ/ሰብ ክፍሎች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ወጣቶቹ ቀዳሚዉን ስፍራ ይይዛል፡፡
    o በገጠርም ሆነ በከተማ በድህነት የሚሰቃዩ ወጣቶች ቁጥር በርካቶች ናቸው፡፡ በየአከባቢው ትምህርት (10ኛ፣ 12ኛ፣ የኮሌጅ እና የዩኒቨርስቲ) ጨርሰዉ ስራ ያላገኙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ብዙ ናቸዉ፡፡ ከ10ኛ ክፍል አንስቶ እስከ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ድረስ ያለዉ የተማረ የሰዉ ሀይል ከ450ሺ እስከ 500ሺ ያህል እንደሚሆን ነባራዊ ሁኔታዉ ብቻ ሳይሆን ተጨባጩም ያው ነው፡፡ ስለሆነም በክልሉ ዉስጥ ገጠርም ሆነ ከተማ ያሉ ወጣቶች ድሀ ብቻ ሳይሆኑ ተስፋ የቆረጡም ናቸዉ፡፡
    o ይህ አሃዝና ሁኔታ በገጠር መጠነኛ መሬት ኖሮት በእርሻ ተግባር በተለያየ ምክንያት ምርታማ ያልሆነ እና በዚህ የተነሳ ወላጆቹንና ቤተሰቡን መመገብ ያልቻለ ወጣትንም ያጠቃልላል፡፡
    እንደ ሀገር ስራአጥ የሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ በማድረግ እነዚህን ወጣቶች ከወላጆች ጫንቃ ላይ ለማላቀቅ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችና የተለያዩ ፓኬጆች ተቀርፀዉ ባለፉት ዓመታት ጥቅም ላይ ዉሏል፡፡ እነዚህ ፓኬጆችና ስልቶችም በሲዳማ ክልል ውስጥ የሚሰሩና የሚተገብሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን የአመራር ስርዓቱ የተበላሸ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ወጣቶች የስራ ዕድል እያገኙ አይደሉም፡፡
    o ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ ሙያዎች ተመርቀው ምንም አይነት የስራ እድል አጥተው በቤታቸው የተቀመጡ ወጣቶች በርካቶች ናቸው፡፡ በሚቀርቡ ብድር አማራጮች የአመራር ቤተሰቦች እና የሀብታሞች ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡
    o የውሸት ሪፖርት የምያደነቁረው ወጣትና ወላጅ ቤተሰብ በቁጥር ብዙ ነው፡፡
    5.2.2 ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮችና አስተሳሰባቸው ሁኔታ
    በሲዳማ ክልል ያሉ ወጣቶች፣ በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ስራ ከማጣት በተጨማሪ የማህበራዊ ጠንቅ ተጋላጭ የመሆን እና የሲዳማ ህዝብ ባለውሌታ የሆነውን የብልጽግና ፓርቲን እየሸሹ ሌላ ፓርቲ ወደ መመስረት ገብተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ክፍል በተወሰነ ደረጃ ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
    o ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶች በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶች የስራ እድል ካለማግኘታቸው እና አስተዋሽ የመንግስት አካል በማጣታቸው የተነሳ አንድም ተስፋ ቆርጠዋል ፣ በሌላ በኩል በወላጆቻቸውም ላይ ሸክም የመሆን እድል ገጥሟቸዋል፡፡
    o በሲዳማ ክልል ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የአስተሳሰብ ብዛሃነትን፣ የልዩነት ሀሳቦችን ለማራመድ የሚመች አይደለም፡፡ በየደረጃው ያለ አመራር የተቃርኖ አስተሳሰብ የሚራምድ ማንኛውንም ግለሰብ አያበረታታም ወይም የተሳሳተውን አስተሳሰብ በትክክለኛው እንድተካ አያደርግም ወይም አያታግልም፡፡ ይልቁንም፣ እንደዚህ አስተሳሰብ ያላቸውን ወጣቶች ማሳደድና ማሸማቀቅ ቁልፍ ተግባሩ ነው፡፡ ከዚህ በተነሳ ወጣቶቹ ሌላ አማራጭ እንድያማትሩና እንድያስቡ እድል እየፈጠረላቸው ይገኛል፡፡ ባለውሌታ የሆነውን የብልጽግና ፓርቲ ወደጎን በመተው ሌላ ፓርቲ እንድመሰርቱም እድል እየፈጠረላቸው ይገኛል፡፡ ይህም የክልሉ ከፍተኛ አመራር ውድቀት እንደሆነ መያዝ አለበት፡፡
    o በሌላ መልኩ ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች አልባሌ ቦታ መዋል፣ አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች መሆን እና ሌሎች ጾታዊ ተፅዕኖዎች ስር መውደቅ ይታያል፡፡ ወጣት ወንዶችም ሆነ ወጣት ሴቶች ኑሮን ለመግፋት የማይገባቸውን ተራራ ስገፉ ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ አመራሩ ውድቀት ነው፡፡
    5.3 የፍትህና የደህንነት ችግሮች
    በሲዳማ ክልል የፍትህንና የፀጥታ ወይም የደህንነት ጉዳዮችን ስንተች፣ ከፍተኛ አመራሩ ያሉብንን ችግሮች በእኛ ጎን ሆኖ እንደሚፈታል እና እንደሚያታግለን በመተማመን ነው፡፡
    በክልሉ ያለው የፍትህ ስርዓት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያስከብር አይደለም፡፡ የፍርድ ቤት ዳኞች ፖለቲከኞች እና አድሎ የሚፈጽሙ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ያልፀዱ ናቸው፡፡ አቃቤ ህግ ባለሙያዎች ፍትህን ለማስፈን ሳይሆን የሹመኞች ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት የተቀመጡ ፣ መርማሪ ፖሊሶች ደግሞ የተዛባ ምርመራ አጠናቅረው ፍትህን ለማዛባት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡
    የየደረጃው የፖሊስ መዋቅር (የወንጀል መከላከል፣ የትራፍክ ፖሊስ አባላት) ወንጀልን ለመከላከል ሳይሆን የወንጀል ድርጊትን ለማበራከት የተመደቡ ይመስላሉ፡፡ የፖሊስ አባላት ከሌቦች ጋር የሚተባበሩ፣ የምያሰርቁ፣ ዜጎችን የሚደበድቡ፣ ግለሰቦችን አርብ አስረው ሰኞ ጠዋት ቃላቸውን የሚቀበሉ እና ግፍ የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ንፁሃን ዜጎችን አፍነው በመውሰድ በወታደር ካምፕ የሚያስሩና የሚደበድቡ ኃይሎች ናቸው፡፡
    የክልሉ የሰላምና ፀጥታ መዋቅሩ በክልሉ ውስጥ የሚሸማቀቅና በስጋት ተሸብቦ የሚንቀሳቀስ ዜጋ እንዲፈጠር ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የራሱን ኔትወርክ ዘርግቶ እገሌ ይፈለጋል፣ እገሊት ትፈለጋለች ወዘተ እያለ ያሳድዳል፣ አሳስሮ ለሁለትና ሶስት ወራት በማረሚያ ቤቶች ያቆያል፡፡ በስተመጨረሻ ክሳቸው ተቋርጧል ይባልና በነጻ ይለቀቃል፡፡
    ከክልል ጀምሮ በየደረጃ ያሉ ዳኞች ዜጎችን የሚጎዳ ውሳኔ ይወስናሉ፡፡ ለማሳሌ፡- በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን ከ3 ዓመት በታች እንዲቀጡ የመወሰን ሁኔታዎች የተለመዱ ናቸው፡፡ አስክረንን አስቀምጠው የመደራደር አይነት አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡
    የጸጥታ መዋቅር የተጣለበትን ህገ መንግስታዊ ግዴታ ወደጎን በመተው ህገወጥ የስለላ መረቦችን በመዘርጋት ከፍተኛ አመራሩን ሊቃወሙ ይችላሉ ወይንም ብልሹ አሠራሮችን አደባባይ ልያወጡ ይችላሉ ተብለው የሚገሙቱ ግለሰቦችን የተለያዬ የጥፋት አካላት ታርጋ በመለጠፍ “የኦኔግ ሸኔና የህወሀት አባሎች ናቸው” በማለት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያለማንም ከልካይ ወከባ፣ እስራትና ድብደባ ይፈጸምባቸዋል፡፡
    5.4 የከተማ ልማት፣ንግድ፣ የፋይናንስ እና ገቢ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች፤
    የከተማ ልማት ስራዎች በየከተሞቹ ያሉ ፍላጎቶች በተለያየ መንገድ የሚገለፁ ቅራኔዎችን የሚፈታ መሆን አለበት፡፡ በከተማ ከፍተኛ የሆነ ድህነት አለ፡፡ ከተሞች እንደየእድገታቸው ልክ በእውቀትና በእቅድ ካልተመሩ ለስርዓቱ አደጋ እንደምሆኑ አያጠራጥርም፡፡
    የክልላችን አመራሮች እነዚህንና ሌሎች የከተማ ልማት ስራዎችን በተሳለጠ መንገድ መርቶ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀመጠ ሳይሆን የከተማ መሬትን በኢንቨስትሜንት ሽፋን ፣ በልማት ተነሺዎች ስም እና በሌሎች ምክንያቶች እየቸበቸበ ፣ አንድም ለራሱ የሚወስድ እና በሌላ መንገድ ደግሞ ለዴላሎቹ የሚያድል ኃይል ነው፡፡
    የከተማ ልማት ስራ ስፋት ያለውና እንደግብርና ልማት ስራ ትርጉም ባለው መልኩ መመራት ያለበት ነው፡፡ በተቋሙ ውስጥ በየደረጃው በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሌብነቶች አሉ፡፡
    o በየወረዳ ያሉ ማዘጋጃ ቤቶች መጻእ እድላችንንና የእድገት ሁኔታችንን ታሳብ ባደረገ መልኩ በእቅድ እየተመሩና እያደጉ አይደሉም፡፡
    o UIDP እና መሰል ፕሮጀክቶች ስም የሚመጡ በጀቶች የዘርፉ አመራር እና በየደረጃ ያሉ ግልሰቦች በተለያየ ምክንያት የሚቀራመቱበት መሆኑ ፤
    ከተሞች በብዙ ችግሮች የተከበቡ፣ በአግባቡ ከተመሩ ደግሞ መልካም እድሎች ያሉባቸው የፖለቲካና የአስተዳደር ማዕከላት ናቸው፡፡ በየከተማው ቅሬታዎች ይኖራሉ፣ ብዛሃ-ፍላጎቶችም አሉ፡፡ እነዚህን ፍላጎቶች አመጣጥኖ መምራት፣ በየአከባቢው የሚፈጠሩ ቅሬታዎችንም በብስሌት ለመፍታት የሚያስችል ስርዓትን ገንብቶ መምራት ወሳኝ ይሆናል፡፡ በሌላ መልኩ ከተማን ለመምራት በተነጻጻር እጄ ንፁህ መሆንንም ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የፊት አመራሮችን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት በሌብነት መረብ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡
    o በልማት ተነሺዎችና በኢንቬስትሜንት ስም ውድ የሆነውን የህዝብ ሀብት (መሬትን) መዝረፍ ይታያል፡፡ ለአብነት፡- 185 የኢንቨስትሜንት ቦታዎችን በዴላላዎች አማካይነት በማዘጋጀት ከእያንዳንዱ ግለሰብ 1,000,000 ብርና ከዚያ በላይ ጉቦ በመሰብሰብ መቀራመት(በዚህ ቅርሚት ውስጥ የክልሉ የፊት አመራሮች አሉበት)፤ ሌሎች አብነቶችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
    የሀዋሳ ከተማ የመሬት ዝርፊያ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የገቢ አሰባሰብም ችግር ያለበት ነው፡፡ ከተማው በራሱ ገቢ ሰብስቦ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ይሰራል፡፡ ይሁንና በዘርፉ ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ሌቦች በመሆናቸው የቫት ቁጥጥርን ጨምሮ የሪስክ ኦዲትና ካፒታል ጋይን አስተዳደር በሌብነት የታጀበ ነው፡፡ የገቢ አወሳሰንና አሰባሰብ ስርዓት ለድርድር የተመቸ እና ባለሙያዎች በስተኋላ የሚደራደሩበት ነው፡፡
    የክልሉ ውስን የሆነው በጀት ለዝርፊያና ለሌብነት የተጋለጠ መሆኑን የክልሉ ኦዲት መ/ቤት በተደጋጋሚ በምርመራው አረጋግጧል፡፡ ለአብነት:- በ2013 የክልሉ ዋና ኦዲት መ/ቤት ባደረገው የሂሳብ ምርመራ 2.8 ቢሊዮን ብር መመዝበሩንና የ2014 በጀት ዓመት ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር በድምር 4.4 ቢሊየን መሆኑ ተረጋግጧል::
    በመንግሥት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር የሚፈጸሙ ምዝበራዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ ትራንስፖርተና መንገድ ልማት፣ ዉሃ ማዕድንና ኢኔሪጂ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ፣ ጤና ቢሮ እና በሌሎችም መ/ቤቶች ያለጨረታ እና ጨረታም ቢኖር በማስመሰል ለአንድ ኮንትራክተር ለመስጠት ከተፈለገ ብዙ ሰው እንደተጫረተ ተደርጎ እንድያሸንፍ ማድረግና በተጨማሪ ስራ ሰበብ ተመሳሳይ የሆኑ ግለሰቦች በተደጋጋሚ እንዲወስዱ ከበላይ አመራር ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመስጠት ውስን የሆነው የክልሉ ሀብት እንድመዘበር እየተደረገ ይገኛል፡፡
    ሌላው ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ደባ ነው፡፡ በሲዳማ ውስጥ ሁለት የኮንትሮባንድ በሮች /መስመሮች/ አሉ፡፡ አንደኛው በሆኮ ወረዳ ዉስጥ የሚገኝ የ’መልካ ደስታ’ በር ሲሆን ሁለተኛው በማጭሾ አድርጎ በጩኮ በኩል ሀዋሳ የሚገባው የ’ጩኮ’ በር ወይም መስመር ነው፡፡ እነዚህ የኮንትሮባንድ በሮች በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ መሪነት የሚጠበቁና በላይነት የሚመሩ በሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ በሮች የሚሸመጠጡ ገንዘቦች ብዙ ቦታዎች የሚደርሱ ናቸው፡፡ የበርካታዎችን ጎሮሮ የሚሸፍን እንደሆነ ይታወቃል፡፡
    የኮንትሮባንድ ጉዳይ በክልሉ ውስጥ ህጋዊ እውቅና ያለው ይመስላል፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ይህንን ጉዳይ እንደ ክስ ገንዘብ ይመለከታል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ለመታገል የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ይደፈጥጣል፡፡
    o ይባስ ብሎ ‘ኮንትሮባንድ የሲዳማ መደበኛ በጀት ስላልሆነ ሲዳማን አይጎዳምና ምን ያስጮሃችኋል” በማለት ያሸማቅቃል፡፡
    o በድፍረት ታግለው የኮንትሮባንድ እቃዎችን የሚያስይዙ ሰዎች ስቃያቸውን ያያሉ፡፡ ለዝርፊያ የማይተባበሩ የጸጥታ ኃይል አባላት ላይ የተለያየ ስያሜ ይሰጣል፤ ግማሹን ወደ ወይኒ ቤት እንድወረወር ይደረጋል፣ ሌላውን ከሥልጣን ዝቅ ማድረግና ከቦታ ማዛወር፤
    ለዚህ አይነተኛ አብነት የሚሆነው በ2014 ዓ/ም ከዳራ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ግምቱ 4.8 ሚሊዮን የሚሆን የታጠበ ቡና ህገወጥነቱ በክልሉ ቡና ግብረ ኃይል ተረጋግጦ እንዲወረስ ውሳኔ የተላለፈውን በማንአለብኝነት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ጉቦ ተቀብሎ በነጠላ ደብዳቤ ያለ ግብረ ኋይሉ ዕውቅና እንድለቀቅ አድርጓል፡፡
    ሌላው የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ቢሮ ያለው ችግር ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ የሲሚኒቶ ንግድ፣ የዘይትና ስኳር፣ የዱቀት አቅርቦት ወዘተ ጉዳዮች በሌብነት ሰንሰሌት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሀቂ ለማውራት የክልሉ ከፍተኛ አመራር በተጨባጭ በንግድ ስራዎች ላይ የተሰማራ ነው፡፡ በጣም ከፍተኛ ሌብነት አለ፡፡
    5.5 የብልፅግና ፓርቲ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚመለከት
    በዚህ ንዑስ ክፍል ስር ለማንሳት የወደድነው ነገር፣ በሲዳማ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ብልሽቶችን ለሚመለከተው አካል በመጠቆም በችግሮቹ ዙሪያ መፍትሄ እንዲሰጥበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያለው፣ ለመብቶቹ መከበር የሚታገል፣ ግዴታዎቹንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ህብረተሰብ ያስፈልገናል፡፡ ህገመንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ መሪዎቹን የመሾምና የመሻር እድል ያለው ህዝብ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ወሳኝነት አለው፡፡ በድምሩ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቹ የተከበሩለት ህዝብ፣ ግዴታዎቹንም ጠንቅቆ በማወቅ ለህግና ለስርዓት ተገዥ መሆን የቻለ ህብረተሰብ ለአንድ ሀገርና አከባቢ መለወጥ ቁልፍ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ሀሳብ ላይ ተመስርተን በሲዳማ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን አጠር አጠር አድርገን ለማስቀመጥ ነው፡፡
    በመሰረቱ በሲዳማ ክልል በየደረጃው ላሉ ችግሮች በዋናነት ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ እና በእሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ለምን? ምክንያቱም የፓርቲው ቁልፍ ተግባር አባላትን ማታገል፣ አቅማቸውንና አስተሳሰባቸውን መገንባት፣ ለክራይ ሰብሳብነት የተመቸ አከባቢ እንዳይፈጠር ወይም ከተገኘም በሰላ ትግል የማረም ስራ መስራት፣ በየዘርፉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለቅሞ በመለየት እንድፈታ ማድረግ ወዘተ ጉዳዮች ናቸው፡፡
    የፓርቲ አመራር ከመንግስት ክንፍ አመራር ክስ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ የፓርቲው አመራር በመንግስት ጉያ ውስጥ ከተወሸቀ እና ስራዎችን በትግል መምራት ካልቻለ ነገሩ አከተመ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም፣ የሲዳማ ክልል የፓርቲ አመራሮች ከግራም ከቀኝም ነጻ አይደሉም፡፡ ሌቦች ናቸው፣ ለሌቦች ሽፋን የሚሰጡም ናቸው፡፡ ወጣቱንም ሆነ መላውን ህዝብ የሚያታግሉ ሳይሆን የምያሸማቅቁ ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ሲዳማ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ እና ኩርፊያ በገጠርም ሆነ በከተማ ተፈጥሯል፡፡
    ሀገራዊ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ በሲዳማ አከባቢም ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡ ለዘመናት ታፍኖ የቆየው ክልል ሆኖ የመደራጀት ህገመንግስታዊ ጥያቄ ሰሚና አድማጭ አካል አግኝተው በአደባባይ የንቅናቄና የትግል አጀንዳ ሆኖ አልፏል፡፡ በዚህም የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ህዝብን የዘመናት ጥያቄን የመለሰ ብቸኛና ባለውሌታ ፓርቲያችን ነው፡፡
    “የብልፅግና ፓርቲ የህልውናችን መረጋገጥ ዓይነተኛ ድርጅት ነው፣ ከዚህ በኋላ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እንሞታለን፣ የደምና የአጥንት ዋጋ እንከፍላለን” ወዘተ የሚሉ አቋሞችንና ስሜቶችን ስያራምዱ የነበሩ የተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች በፍጥነት ተስፋ በመቁረጥ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችላቸውን አቋም ማራመድ የጀመሩት ገና ከክልል ምስረታ ማግስት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መላ ወጣቶችንና የተለያዩ ህ/ሰብ ክፍሎችን ያንቀሳቀሰ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ተመስርቶ በክልሉ የበርካታ አባላቶች ባለቤት የመሆን እድል አግኝቷል፡፡
    ከመድብሌ ፓርቲ ስርዓት አንጻር ሌላ ፓርቲ መመስረቱ ችግር ባይኖረውም፣ የሲዳማ ህዝብ ለፓርቲያችን ካለው መልካም ግምትና ስፍራ አኳያ መመስረቱ የሚገባ አልነበረም፡፡ የመመስረቱ ስህተት በዋናነት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሮችን ጨምሮ የየደረጃው መዋቅር ውድቀት እንደሆነ መያዝ አለበት፡፡

አባሪ …
 የሁለቱ ቱባ አመራሮች ሌብነትና ብልሹ ድርጊታቸው በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ አካላት እንድቀርብ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡ ጉዳዮች ሁሉቱንም ግለሰቦች ይመለከታል፡፡

  1. የአቶ ደስታ ሌዳሞ ቡላሞ ሌብነትና ብልሹ በሚመለከት የቀረበ መረጃ
     ይህ ግለሰብ እድሜ ልኩን የመንግስት ሰራተኛና ተሿም ሆኖ እያገለገለ የቆየ ሲሆን ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ያካበተ/ የፈጠረ መሆኑን ለመንግስት ለመጠቆም ነው፡፡
     ግለሰቡ በህይወት ዘመኑ በመንግስት ሠራተኝነትና ተሿም በመሆን ያሳለፈ ቢሆንም መንግስት ያወጣውን ከፍተኛ አመራሮችና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚለውን መመሪያ በመከተል 86,000,000.00 (ሰማኒያ ስድስት ሚሊየን) ጥሬ ገንዘብ እና 250,000,000.00 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሚሊየን ብር) የሚያወጣ ሀብት እንዳለው በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስመዝግቧል፡፡ ለመሆኑ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ይህን ሁሉ ሀብት ከየት አመጣው?
     በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በቅርቡ ሁለት ሄክታር መሬት በኢንቨስሜንት ስም የወሰደ መሆኑ፤
     በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ክ/ከተሞች በህገወጥ መንገድ የወሰደበት መሬቶች ያሉት መሆኑ፡- ለአብነት በመነኃሪያ ክ/ከተማ ጉዌ ስታዲም ቀበሌ በተለምዶ ዋናዛ አደባባይ አከባብ በ300ካ/ሜ ላይ ያረፈ ይዞታ፣ በተመሳሳይ በዚሁ ቀበሌ በ800ካ/ሜ ላይ ያረፈ ቅንጡ የመኖሪያ ቤት ያለው መሆኑ፣ አሁንም በመነኸሪያ ክ/ከተማ ጉዌ ስታዲየም ቀበሌ አላትዮን ሆስፒታል አጠገብ 2000ካሜ መሬት ያለው መሆኑ፣ በምስራቅ ክ/ከተማ ሳሙኤል ገበያ አደራሽ አጠገብ ያለው 800ካ/ሜ ይዞታ፣ በታቦር ክ/ከተማ ወ/አማኑኤል አደባባይ አጠገብ 400ካ/ሜ ይዞታ ላይ ያረፈ የንግድ ቦታ ያለው መሆኑ፣ በተመሳሳይ በዚሁ ክ/ከተማ ፋራ ቀበሌ ውስጥ 1200ካ/ሜ ይዞታ ላይ ያረፈ ህንጻ(ይህ ህንጻ በአሁኑ ወቅት ለክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጅ ቢሮ ያለ ጨረታ በእሱ ትዕዛዝ ለቢሮነት እንዲከራዩት ተደርጎ በዓመት 7 ሚሊዮን የሚያገኝ መሆኑ)፤ አሁንም በታቦር ክ/ከተማ ሂጣታ ቀበሌ ዶሮ እርባታ መንደር 400ካሜ ላይ ቪላቤት ተገንብቶ ያለው መሆኑ፤
     በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ የልማት ተነሽ ያልሆኑትን ምንም ይዞታ የለላቸውን በልማት ተነሽ ስም በፓስተር ሄኖክ ባናታ እና ባለቤቱ ስም 2 የፕላን ቦታ፣ በአቶ ጋሊፋቶ /ዘመዱ/ አንድ የፕላን ቦታ የወሰደ መሆኑ፤ በተመሳሳይወ/ሮወዩ ጠካሞ፤ወ/ሮ ዘነበች ቀራ፣ ጡኒ በቀሌ፣ ወ/ሮ ሄሊሴ፣ ወ/ሮ ዲካሼ፣ ወ/ሮ ወርቄ፣ ወ/ሮ በላይነሽ፣ አቶ ማርቆስ ሉንጨሳ፣ አቶ ተሰማ፣ ወ/ሮ ማሳናቱ ዳጋላ ስም፣ በድምሩ 10 ፕላን የወሰደ ሲሆን ቦታው በፋራ ቀበሌ በተለምዶ አጠራር ከብት ገበያ እና ሞኖፖሊ አካባቢ የተወሰደ ነው።
     በተጨማሪም በአቶ ያረድ በቀለና ባለቤቱ፤አሰፋ አጋሮ ስም በጫፌ ኮትጃዌሳ ቀበለ አድስ በተሸነሸነ ቦታ ለግለሰቦቹም በሌላ ሰዉ ስም እንዲውዱ በማድረግ በግሌሰቦቹ ስም ወስደዋል፡፡
     ከእሼት ቡና እንዱስትሪ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የዞን አስተዳዳሪ በነበረበት ወቅት ወቅቱ ለነበረው ግብርና ኃላፊ ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት ከአሰራር ስርዓት ውጭ በቁጥር 29 የእሼት ቡና ኢንዱስትሪ ፈቃድ እንዲሰጥ አድርጓል፤ በተመሳሳይ 2014 ዓ.ም አሰራር ስርዓቱን ባልተከተለ መልኩ ምንም ዓይነት የአዋጭነት ጥናትና የአከባብ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይደረግ ፣ምንም እንኳን ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነትና ስልጣን የግብርና ቢሮ ሆኖ ሳለ ያንን በጉልበት በመንጠቅ 42 ኢንዱስትሪዎች ለግለሰቦች በመስጠት ከእያንዳንዳቸው ከአንድ ሚሊየን እስከ አምስት ሚሊየን ብር ፣ በድምሩ 144 ሚሊየን በላይ ብር ጉቦ ሰብስቦ በመውሰድ በክልሉ ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ያደረገ ስሆን ከተፈቀደላቸው ከ42ቱ ውጭ በቁጥር 8 የሚሆኑ የቡና ኢንዱስትሪ ሳይቶች አስቀድመው ግንባታ ካጠናቀቁ በኋላ በድርድር ፣ በቤተቦቹ ስም ሼር በመግባት የኢንዱስትሪ ባለቤት ሆነዋል፡፡
     የተለያዩ ጉባኤዎችንና የመስክ ምልኬታዎችን በማድረግ ከእያንዳንዱ ሴክተር ቢሮዎች እና ከ36ቱ ወረዳዎች ውድድርና ፉክክር በሚመስል መልኩ ከ110 እስከ 150 ግራም ወቅር እና ከድሃው አርሶ አደር እጅ በመንጠቅ የምታለቡ ላሞችን በስጦታ መልክ እየዘረፈ የሚገኝ ስሆን ወደ ገንዘብ ስቀየር ከ50 ሚሊየን በላይ ይሆናል፡፡
     ግለሰቡ ክልሉን መምራት ከጀመረ ወዲህ የመንግስት ፋይናንስን ለዘረፋ በሚመች መልኩ ስለመራው 4.4 ሚሊየን ብር በተለያየ መንገድ የተመዘበረ መሆኑን የክልሉ ኦዲት ቢሮ አረጋግጧል፡፡
     አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ (G+3)ህንፃ መኖሩ፣
  2. አቶ አብርሃም ማርሻሎ ኢትሶ ሌብነትና ብልሹ በሚመለከት የቀረበ መረጃ
    ይህ ግለሰብ እድሜ ልኩን የመንግስት ሰራተኛና ተሿም ሆኖ እያገለገለ የቆየ ሲሆን ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ያካበተ/ የፈጠረ/ መሆኑን ለመንግስት ለመጠቆም ነው፡፡
    • በሎካ አባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ በሰራበት ወቅት በወረዳዉ ዋና ከተማ 14 የንግድና የመኖሪያ ቦታ በራሱና በበተሰቡ ስም የወሰደ መሆኑ፤
    • አመራር ሆኖ ሳለ በዚያ ወረዳ በቡክቶ ቀበለ 560 ሄክታር የእንቬስትመንት መሬት መዉሰዱ፤
    • በይርጋዓለም ከተማአስተዳደር በፊልዉሃ ቀበለ ቅንጡ የመኖሪያ ቤት የገነባ መሆኑ፤
    • በሐዋሣ ከተማ ታቦር ክ/ከተማ ፋራ ቀበለ ቅንጡ የመኖሪያ ቤት የገነባ መሆኑ፤በተጨማሪም በዚሁ ክ/ከተማ ሂጣታ ቀበለ በ200 ካ/ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ቤት ያለዉ መሆኑ፤
    • በደቡብ ክልልና በሲዳማ ክልል አመራርነት ዘመኑ የሀዋሳ መሬትና የጋራ መኖሪያ ቤት በልጁና በምስቱ ስም በመዉሰድ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ያፈራ ስሆን ለአብነት ፤በልጁ ስም የጋራ መኖሪያ በቶች በደቡብ ኢዝ ሳይት አራት ቤቶችን ወስዶ መሸጡ፤
    • በ2011 ዓ/ም በሐዋሳ ከተማ በልማት ተነሽ ስም በባለቤቱ በወ/ሮ አስቴር ጋቢሶ ስም በተለምዶ አጠራር ዶሮ እርባታ በሚባል መንደር 2 መሬት መዉሰዱ፤
    • በተመሳሳይ በልማት ተነሽ ስም በጨፌ ኮትጃዌሳ ቀበሌ በአካል በለለ በግዴ መሹ በምባል ስም 200 ካሬ መዉሰዱ፤
    • አሁንም ለቄራ አገልግሎት የልማት ተነሺዎች ሲነሱ 3 ግለሰቦች ስም በማካተት የ5ኛ ዙር የልማት ተነሽ ስም መዉሰዱ፤
    • በአድስ አበባ በቦሌ ክ/ከተማ በሚስቱ አስቴር ጋቢሶ ስም በ46 ሚሊዮን ብር G+3 ፎቅ ቤት መግዛቱ፤
    • በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሂጣታ ቀበሌ በተለምዶ 7ኛ ካምፕ አከባቢ በእነ ተስፋዬ በልጂጌ ሰፈር G+2 የመኖሪያ ቤት ያለው መሆኑ፤

ማጠቃለያ
በሲዳማ ክልል ያሉ ችግሮች በዚህ ሰነድ ብቻ ተሰንደው የሚያበቁ አይደሉም። በሂደት የሚወሰዱ እርምጃዎችም ይሁን ለሚመለከተው አካል የምሰጠው ጥቆማ አሊያም መረጃ የሚቆም አይሆንም። በመሆኑም የችግራችን ስፋትና ጥልቀት ከፍ ባሉት ክፍሎች ከተገለፀው በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ትግላችን በዚያው ልክ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
በክልላችን ያሉ መሰረታዊ ችግሮች ብዙ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ ሌብነት፣ የወጣቶች ስራ ማጣት፣ የአመራር ውጤታማነት ችግሮች፣ የአመራር ምደባና ስምሪት ችግር ያለበት መሆን፣ የማህበራዊ ዘርፍ ልማት ትኩረት የተነፈገው መሆን፣ ጫፍ የወጣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
የሲዳማ ክልል አመራር ሁኔታ ፣ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን መዋቅራዊ በደልና ሌብነት ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፣ የወጣቶች ስራ አጥነትና ማህበራዊ ጠንቅ ተጋላጭነታቸው ወዘተ ጉዳዮችን በዚህ ሰነድ ለማስቀመጥ ሞክረናል። ከዚህ የተነሳ በክልሉ ውስጥ ተስፋ የቆረጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውንና ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ያለ መሆኑን፣ ይህም ልመጣ የቻለው በክልሉ ከፍተኛ አመራር እንዝላልነት እንደሆነ በስፋት አስቀምጠናል።
በመጨረሻም በዚህ ሰነድ አማካይነት ያቀረብናቸው ጉዳዮች የሲዳማ ክልል ነባራዊ እና ህሊናዊ ሁኔታዎችን የሚያመላክቱ ናቸው።

ታህሳስ 2015 ዓ.ም
ሀዋሳ ፣ ሲዳማ


Discover more from Sidama Crisis Monitor

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Leave a comment

Discover more from Sidama Crisis Monitor

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading